ይቅርታ ጠይቀው ይመለሳሉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ይቅርታ ጠይቀው ይመለሳሉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- መጋቢት 17/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባን ልማት ሳይመለከቱ አቃቂር የሚያወጡ አካላት በሂደት ለውጡን ተረድተው ይቅርታ ጠይቀው ይመለሳሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶችን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ ፤ “ብዙዎች አቃቂር የሚያወጡ ሰዎች አዲስ አበባ ያልመጡ ናቸው” ብለዋል።

እነዚህ ሰዎች ባሉበት ሆነው ስለ መፈናቀልና ስለ ሰላም ማጣት ቢሰብኩም፤ በሂደት ለውጡን ተረድተው እና ይቅርታ ጠይቀው እንደሚመጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማቱ ከመንገድ ግንባታ ባለፈ በፊት ከነበረው በእጥፍ የሚበልጡ የመዲናዋን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያነቃቁ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላትና ሱቆች የተገነባበት እንዲሁም ለብዙዎች የስራ ዕድልን የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማንኛውም ልማት ሙሉ በሙሉ ከችግር የጸዳ ሊሆን እንደማይችል ገልጸው ፤ በኮሪደር ልማቱ ወቅት የሚታዩ ለውጦች አካባቢን ለተሻለ አገልግሎት ከማዋል ጋር የተያያዘ እንጂ “ሰው ማፈናቀል፣ መጉዳት አይደለም” ሲሉ አሳስበዋል።

በዋዛ ፈዛዛ የሚገነባ ሀገር የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚፈጠሩ ስህተቶች ካሉ የልማቱ ዋና ዓላማ ሀገርና ህዝብ ስለሆነ “እናርቃለን፣ እናርማለን፣ እናሻሽላለን” ብለዋል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ጩኸት እንደማያቆመው እና እያንዳንዷ ሰከንድና ደቂቃ የሀገሪቱን ብልጽግና በሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ እንደሚውል በአጽንኦት ተናግረዋል።

በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ሀገር ስታድግ የማይጠቀም ዜጋ እንደማይኖርና ሁሉም በአንድነት ለሀገር ግንባታ እንዲቆም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review