AMN-መጋቢት 17/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ አራተኛው “Invest in Ethiopia 2026” የቢዝነስ ፎረም ተጀምሯል።
ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ብቻ አይደለችም፤ ዛሬ በፈጣን የለውጥ ጎዳና ላይ ያለች፣ ግዙፍና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ እየገነባች የምትገኝ ሰፊና አዋጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት መሶባችን በትጉኅና ወጣት ሕዝብ ዐቅም፣ ባልተነካ የተፈጥሮ ጸጋ እና በስትራቴጂያዊ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የታደለ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል ።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርማችንና በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያችን ለዘመናዊና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ የማይመቹ አሠራሮችን በቆራጥነት በመቀየር እንደ ፋይናንስና ቴሌኮም ያሉ ቁልፍ ዘርፎችን ለዓለም አቀፍ ኢንመስትመንት ክፍት መደረጋቸውንም ነው አቶ ተመስገን የገለፁት ።
የመሠረተ ልማት አውታሮችን ማስፋፋታችንና የሕዳሴው ግድብን በማጠናቀቅ አስተማማኝ የኃይል ምንጭ መፍጠራችን ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ ምኅዳርና ቁርጠኝነት ለዓለም የሚያረጋግጡ ታላላቅ ማሳያዎች ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
እኛ የምንፈልገው ድጋፍን ሳይሆን አጋርነትን ነው፤ እርዳታን ሳይሆን ኢንቨስትመንትን ነው! ለባለሀብቶች ምቹ፣ ግልጽና ተራማጅ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅተናል ያሉት ምከትል ጠቅላይ ሚኒስርት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚረጋገጠው በግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ፣ በፈጠራና በርትዕ በሚመራ የኢኮኖሚ ምኅዳር መሆኑን በጽኑ እናምናለን ሲሉ ነው የገለፁት ።

አቶ ተመስገን ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ካፒታል፣ ለችሎታ እና ለዕድል በሯን ወለል አድርጋ ከፍታለች የዛሬው መድረክም ራዕይን ከተግባር፣ ዕቅድና መሻትን ደግሞ ከኢንቨስትመንት ጋር በማገናኘት የጋራ ብልጽግናችንን የምንቀርጽበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለዋል ።
ኢትዮጵያ አሁን በፍጥነት ወደ ከፍታ እየገሠገሠች ባለችበት በዚህ ታሪካዊ የዕድገት ጉዞ፣ ለዓለም አቀፍና ለሀገር ውስጥ ባለ ሀብቶች ኢትዮጵያ ለእናንተ ዝግጁ የሆነ፣ በዕድሎችና በስኬቶች የተሞላ ታላቅ የኢንቨስትመንት መሶብ አላት፤ ኑ አብረን እንሥራ! ሲሉ መልእክታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አጋርተዋል።