AMN መጋቢት 17/ 2018 ዓ.ም
የፓናል ውይይቱን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ መከላከያ የኒቨርሲቲና የመከላከያ ዋር ኮሌጅ በጋራ ሲሆኑ በውስብስብ የደህንነት ምህዳር ወሰጥ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማረጋገጥ ስትራቴጅ ደግሞ የውይይቱ መሪ ቃል ነው።
የፓናል ውይይቱን የከፈቱት የመከላከያ ሚኒስቴር ፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ አለማችን ከነጠላ ልዕለ ሃያል ወደ ብዙ ዋልታ የሽግግር ሂደት እንደምትገኝ ገልፀው ሂደቱ ግን ብዙ ውስብስብና አስቸጋሪ የፀጥታ፣ የደህንነት ሁኔታዎችን ማሥከተሉን አንስተዋል።
ወይዘሮ ማርታ እንዳሉት አሁናዊ የቀጠናው ሁኔታ እድልም ስጋትም ይዞ የመጣ በመሆኑ ፣ እንደ ሀገር ዕድሉን ለመጠቀምና ስጋት ሆነው ለሚመጡ ችግሮች ደግሞ ምላሽ ለመስጠት ዘመኑን የዋጀ ጠንካራ ተቋምና ሀገር መገንባት ያሥፈልጋል።
በተለይ እኛ በምንገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ያለው የሃይል አሰላለፍ ተፅዕኖ እየታየ ያለበት በመሆኑ ከእኛ ብሔራዊ ጥቅም አኳያ አስታርቀን ለመሄድ በሳል የሆነ ስትራቴጅክ መከተል ይኖርብናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ አለም አቀፍ ተለዋዋጭ የጦርነት ባህሪያትን በመረዳት ለአሁናዊ የቀጠናው ችግሮች ፈጣን ምላሽ መስጠት በሚያስችል ቁመና ተገንብቶ መገኘት እንደሚያስፈልግ ገልፀው ተቋማችን መከላከያም በዚህ ልክ ራሱን እያዘጋጀ እንደሚገኝ አሥገንዝበዋል።

ሉዓላዊነቷ የተከበረ ኢትዮጵያን ለመገንባት ውሰጣዊ አንድነትን ማጠናከር አለብን ያሉት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ በዚህም የወጣቶችን የስራ እድል መፍጠርና አዳጊ ኢኮኖሚን መገንባት እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጥላሁን ደምሴ ወይይቱ ለሰራዊታችን ሁለንተናዊ ዝግጁነት አሰፈላጊ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ የሚረዱ ቀጠናዊና አለምአቀፋዊ ሁነቶችን የሚዳስሱ መሰል ወይይቶች እንደሚቀጥሉ መናገራቸዉን የሃገር መከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡