ለሕዝባችን የገባነውን ቃል በተግባር መፈፀም ተከታታይነት ያለው የማያቋርጥ ተግባር ሆኗል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ለሕዝባችን የገባነውን ቃል በተግባር መፈፀም ተከታታይነት ያለው የማያቋርጥ ተግባር ሆኗል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN መጋቢት 17/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ በከተማችን 4ኛውን የቂርቆስ ቅርንጫፍ አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት በይፋ ሥራ አስጀምረናል ብለዋል፡፡

የቂርቆስ ቅርንጫፍ አዲስ የመሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት 20 ተቋማት፣ በ85 የአገልግሎት መስኮቶች፣ 112 የተለያዩ የሕዝብ አገልግሎቶችን በአንድ ስፍራ ለተገልጋይ ያቀርባል።

ይህም የመንግሥት አገልግሎትን በማላቅ፤ ደላላን ፣ ሌብነትን፣ አድሎ እና እንግልትን በማስወገድ፣ ተደራሽነትን እና የዜጎችን እርካታ በማሳደግ፣ በተቋማት መካከል የነበረውን የተበታተነ አገልግሎት በማቀናጀት እንዲሁም ኅብረተሰቡ አገልግሎት ለማግኘት የሚያጠፋውን ጊዜና ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ፍትሐዊ አገልግሎት የሚያሰፍን ይሆናል ብለዋል፡፡

የተቀናጁ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የመንግሥት አገልግሎት አፈጻጸም ቁልፍ የክዋኔ መለኪያ እና አጠቃላይ የዜጎች እርካታን እያመጡ፣ አካታች እና ፍታዊ ተጠቃሚነት ማጎልበቻ ስርአት እየሆሙ ነው። ማዕከሉ ለአጠቃላይ ተገልጋዩ ማህበረሰብ ምቹ ሲሆን፤ በተለይም አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ፣ እንዲሁም ለሠራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢን የፈጠረ ነው።

የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል አቀናጅቶ የማቅረብ መርሃ ግብር ስኬት እና በተሟላ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆን አስቀድመን በኮሪደር ልማት የዘረጋናቸው መሠረተ ልማቶች ወሳኝ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉ።

ይህንን ለሕዝባችን እሮሮ መነሻ ሆኖ የቆየ አገልግሎት አሰጣጥ ችግር መሰረታዊ መፍትሄ ወደ ሥራ እንዲገባ በፍጥነትና በትጋት ሌት ተቀን ለሠራችሁ፣ የሕዝባችንን የአገልግሎት ጫና ላቀለላችሁ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review