AMN-መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
የሰውነት መገጣጠሚያዎች በአግባቡ ተግባራቸውን እንዲወጡ ከሚያስችሉ የሰውነት ክፍሎች መካከል ጉልበት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ወሳኝ የሰውነት ክፍል በተለያዩ ምክንያቶች ለከፍተኛ ህመም እና ለእንቅስቃሴ መገደብ ሊዳረግ ይችላል፡፡
የጉልበት ህመም በድንገተኛ አደጋዎች፣ በሌሎች የጤና እክሎች እና በተሳሳቱ የአኗኗር ዘይቤዎች አማካኝነት የሚፈጠር ችግር መሆኑን የአጥንት ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ናታን ወንድወሰን ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
በተለይም እንደ አጥንት መገጣጠሚያ መላላት እና የመገጣጠሚያ መቆጣት ያሉ የጤና ችግሮች ለህመሙ መከሰት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በደም ውስጥ የዩሪክ አሲድ መጠን መጨመርም በመገጣጠሚያዎች ላይ ከፍተኛ ቁስለት እንደሚፈጥር ዶ/ር ናታን አብራርተዋል።
በተጨማሪም በድንገተኛ አደጋ የሚከሰቱት የጅማት መለጠጥ፣ የመንሸራተቻ አጥንት ስብራት እና የአጥንት መሳሳት ለጉልበት ህመም ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በተለይም ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ውፍረት በጉልበት መገጣጠሚያዎች ላይ የማያቋርጥ ጫና ስለሚፈጥር ለችግሩ ተጋላጭነትን ይጨምራል።
ይሁን እንጂ ይህንን የጤና ስጋት አስቀድሞ መከላከልና የህመም ስሜቱንም መቀነስ የሚቻልባቸው መፍትሄዎች መኖራቸውን ዶ/ር ናታን ጠቁመዋል።
ለዚህም የሰውነትን ክብደት በአግባቡ መቆጣጠር በጉልበት ላይ የሚወድቀውን ጫና ለመቀነስ ቀዳሚው ተግባር ሲሆን፤ እንደ በእግር መራመድ እና የውሃ ዋና ያሉ የጡንቻ ማጠናከሪያ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር የጉልበትን ጥንካሬ ይጨምራል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ለረጅም ሰዓት አለመቆም፣ የሰውነትን ሚዛን የሚጠብቁና ለእግር ምቹ የሆኑ ጫማዎችን መጠቀም እንዲሁም በመገጣጠሚያዎች ውስጥ የሚገኙ ፈሳሾች እንዳይደርቁ በቂ ውሃ መጠጣት ለጉልበት ጤንነት ወሳኝ መሆኑን ዶ/ር ናታን ገልጸዋል።
የጉልበት ህመሙ ከፍተኛ እብጠት ካለው፣ መራመድ ካስቸገረ ወይም የህመም ስሜቱ እየበረታ ከመጣ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የህክምና ተቋም በመሄድ የባለሙያ ምርመራና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ናታን ወንድወሰን አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው