AMN- መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከሳኦቶሜ ጋር ያከናውናል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከዚህ ቅድመ ማጣሪያ ተላቆ ነበር ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያስመዘገበው ደካማ ውጤት ግን በአህጉሪቱ ካሉ ዝቀተኛ ደረጃ ካላቸው 12 ሀገራት አንዱ ሆኖ ወደ ቅድመ ማጣሪያ ተመልሷል።
ይህን ደረጃውን ለማሻሻል እና ወደ አፍሪካ መድረክ ለመመለስ ፌዴሬሽኑ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ቀጥሮ እየሰራ ይገኛል።
ከ11 ዓመታት በፊት የዋልያዎቹ አሰልጣኝ የነበረው ዮሐንስ ሳህሌ ዳግሞ የተረከበውን ሀላፊነት ዛሬ በሚያደርገው ጨዋታ ይጀምራል።
ኢትዮጵያ ከሳኦቶሜ ጨዋታቸውን በሞሮኮ አል ጀዲዳ በሚገኘው አል አብዲ ስታዲየም ያከናወናሉ።
ምሽት 12 ሰዓት እንደሚከናወን በተነገረለት ጨዋታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል አባቱን በሞት አጥቶ ከተለየው ጋቶች ፓኖም ውጪ ሙሉ ስብስቡ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
በዛሬው ጨዋታም ሙሉ ቀይ መለያ አጥልቀው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ተገልጿል።
ሳኦቶሜ ከኢትዮጵያ ዝቅ ያለ ደረጃ ብትገኝም በርካታ ተጫዋቾቿን ከአውሮፓ ነው የጠራችው። ተጫዋቾቹ ምንም እንኳን ዝቅ ባሉ ዲቪዚዮኖች ይጫወቱ እንጂ ለዋልያዎቹ ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ።

ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ተጫውተው አንድ አንድ ድል አስመዝግበዋል።
ለ2018 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በነበረው የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ የተገናኙት ሁለቱ ሀገራት የመጀመሪያውን ጨዋታ ሳኦቶሜ በሜዳዋ 1ለ0 ማሸነፍ ችላ ነበር።
በአዲስ አበባ ስታዲየም የተከናወነው የመልሱን ጨዋታ ግን ኢትዮጵያ በዳዊት ፍቃዱ ፣ ጋቶች ፓኖም እና ራምኬል ሎክ ግቦች 3ለ0 ማሸነፏ ይታወሳል።
በሸዋንግዛው ግርማ