AMN — መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
በተያዘው የበጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግና የውጭ ምርቶችን በመተካት 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን የገለጹት ከተለያዩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የተወጣጣ የጋዜጠኞች ቡድን በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን በጎበኙበት ወቅት ነው።
አቶ ታረቀኝ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ “ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገራዊ ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል።
ባለፉት አምስት ዓመታት መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረትም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ቀደም ሲል ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 66 በመቶ ማደግ ችሏል።
ለዚህ ስኬትም የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን ጨምሮ በዘርፉ የነበሩ ማነቆዎችን ለመፍታት የተከናወኑ የፖሊሲ ክለሳ ስራዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ ፋብሪካዎች ዳግም ስራ እንዲጀምሩ ከማድረግ ባለፈ አዳዲስ ፋብሪካዎች እንዲገነቡ መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።
በዚህም በሀገር ውስጥ ማምረት በመቻሉ ቀደም ሲል ለገቢ ምርቶች ይወጣ የነበረ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ማዳን የተቻለ ሲሆን፣ በአንጻሩ ደግሞ ከአምራች ኢንዱስትሪው የወጪ ንግድ ከ289 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።
እንደ ሀገር የዘርፉን ስኬታማነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የግሉን ዘርፍ በስፋት የማሳተፍ ስራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ታረቀኝ ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚታዩ የአሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍም ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራሮችን ተግባራዊ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
በሔኖክ ዘነበ