AMN — መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
በታሪክ መዝገቦች ላይ ከሰፈሩት እጅግ አስገራሚ እና ለማመን ከሚከብዱ ክስተቶች መካከል የሩሲያዊቷ ቫሲሊየቭ ታሪክ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
ከ1700-1775 ዓ.ም. ድረስ የኒረችው ይህች እናት በሕይወት ዘመኗ 69 ልጆችን በመውለድ የዓለምን ክብረ ወሰን ይዛለች።
ብዙዎቻችን “አንድ እናት እንዴት 69 ጊዜ ትወልዳለች?” ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። ነገር ግን ምስጢሩ ያለው በምጥ ብዛቱ ሳይሆን በአንድ ጊዜ በሚወለዱት ልጆች ብዛት ላይ ነው።
እናቲቱ በጠቅላላው 27 ጊዜ ብቻ ያማጠች ቢሆንም፣ ልጆቹ የተወለዱት ግን አስራ ስድስት ጊዜ 2 መንታ፣ ሰባት ጊዜ 3 መንታ፣ አራት ጊዜ 4 መንታ ሲሆን በድምሩ በ27 ጊዜ ምጥ 69 ልጆችን ተገላግላለች።
ምንም እንኳን ታሪኩ ከሳይንሳዊ እውነታ አንጻር የማይታመን ቢመስልም፣ በወቅቱ የነበሩ በርካታ ታማኝ ምንጮች ግን የክስተቱን እውነተኝነት አረጋግጠዋል።
የኒኮልስክ ገዳም ዘገባ እንደሚያሳየው (የካቲት 27 ቀን 1782 ዓ.ም): ገዳሙ እያንዳንዱን ልደት በዝርዝር መዝግቦ ለሞስኮ ባለሥልጣናት ሪፖርት ያደርግ ነበር።
ዘ ጄንትልማንስ የተባለው የሀገሪቱ መጽሔት እንደዘገበው ደግሞ በወቅቱ በሴንት ፒተርስበርግ ይኖር የነበረ አንድ እንግሊዛዊ ነጋዴ ለቤተሰቦቹ በጻፈው ደብዳቤ፣ አባትየው ፊዮዶር ቫሲሊየቭ በ75 ዓመቱ እጅግ ጤናማ እንደነበረና ለሩሲያዋ እቴጌ ሊተዋወቅ እንደሆነ ገልጿል።
የላንሴት የሕክምና መጽሔት (1878 ዓ.ም) የፈረንሳይ አካዳሚ ባደረገው ጥናት ላይ ይህንኑ የቫሲሊየቭን ቤተሰብ ታሪክ እንደ ትልቅ አብነት ጠቅሶታል።
የሕክምና ባለሙያዎች ስለሁኔው ሲያስረዱ በርካታ ልጆችን እንድትወልድ ያደረጋት ሀይፐር-ኦቩሌሽን የተባለ የሰውነት ሁኔታ ሊሆን እንደሚችል የሚያብራሩ ሲሆን ይህም አንዲት እናት በአንድ የወር አበባ ዑደት ውስጥ ከአንድ በላይ እንቁላል እንድታመርት ስለሚያደርጋት፣ መንታ እና ከዚያ በላይ ልጆችን የመውለድ እድሏን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምረዋል።
አንዲት እናት ለ18 ዓመታት ያህል ስትጸንስ መቆየቷ የእናቶችን ጥንካሬ በሚገባ አያሳይም ትላላችሁ!
በፍሬሕይወት ብርሃኑ