AMN — መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መዲና በመሆን የምትታወቀው አዲስ አበባ፣ ለታላላቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ያላትን ተመራጭነት ዳግም በማረጋገጥ 5ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የህብረተሰብ ጤና ጉባኤን እንድታስተናግድ ተመረጠች።
የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC)፤ ኢትዮጵያ ያላትን ጠንካራ የማስተናገድ አቅምና ደማቅ የእንግዳ ተቀባይነት ልምድ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ይህ ታላቅ ዓለም አቀፍ መድረክ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ወስኗል።
ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በአካል ይገኙበታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ጉባኤ፣ ከተማዋ ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ኩነቶች ያላትን ዝግጁነት በድጋሚ ለዓለም የሚያሳይ ይሆናል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ ይህ ምርጫ አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ከማሳደጉም ባለፈ፣ አገሪቱ በሕብረተሰብ ጤናና በዲፕሎማሲው መስክ የሚያጠናክር መሆኑን ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።