AMN — መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በዝርፊያ ከሀገር ዉጭ ተወስዶ የነበረው የእቴጌ ጥሩወርቅ ዉቤ (የአጼ ቴዎድሮስ ባለቤት) የፀጉር ጌጥን በክብር ተረከበች፡፡
በርክክቡ መርሃ ግብር ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬከተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ) ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር ውጭ የተወሰዱ በርካታ ቅርሶችን ማስመለስ ተችሏል፤ ቀሪዎችንም ለማስመለስ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንብረት የሆኑ ነገር ግን የተዘረፉ ቅርሶቻችንን ለማስመለስ በድርድርም ሆነ በክርክር እስካሁን 72 ቅርሶችን ለማስመለስ ተችሏል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የተዘረፉ ቅርሶችን ለማስመለስ ይረዳ ዘንድ ባለስልጣን መ/ቤቱ ቀደም ሲል በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተዋቅሮ ሳለ ብሔራዊ የቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ተከትሎ ሀገርን የሚያኮራ ስራ ሰርተዋል፣ እየሰራም ይገኛል ብለዋል፡፡
ይህ ቅርስ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትርጉም አለው ያሉት አበባው አያሌው (ረ/ፕ) ከብዙ ልፋትና ውጣውረድ በባለስልጣኑና በኢትዮጵያን ወዳጆች፣ዜጎችና ደርጅቶች ያለሰለሰ ጥረትና ጥምረት ልመለስ ችለዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንጉሳዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት ይህንን ቅርስና ከዚህን በፊትም የአጼ ተዎድሮስ ጋሻ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም ለድርጅቱ፣ ለልዑል ኤርሚያስ ሳህሌስላሴና ባልደረቦቻቸው እንዲሁም ለዶ/ር አሉላ ፓንክርስ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር ውጭ የወጡ ቅርሶቻችንን ለማስመለስ ባለስልጣን መ/ቤቱ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ በትኩረት ይሰራል ሲሉ ዋና ዳይሬክቱ ገልፀዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የባለስልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች፣የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር አባላት፣ የኢትዮጰያ ቅርስ ባለአደራ አባላት፣ የጥንታዊት ኢትዮጰያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ቅርሱን በማስመለስ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱት ግለሰብና ድርጅት የምስጋና ምስክር ወረቀት እንደተበረከተላቸው ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡