AMN – መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ስም “የዲጂታል ካርታ ለማስወጣት ለአመራሮች የሚከፈል” በሚል ከ6 ሚሊየን ብር በላይ በማታለል የተቀበሉ 5 ግለሰቦች ላይ የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ መሰረተ።
የክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች፦
1. ዳዊት መንግስቱ
2. ሳሙኤል ኪዳኔ
3. ቶማስ ማናዬ
4. ፅዮን አበራ
5. ሚኪያስ አውላቸው ናቸው።
እንደ ዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር፣ ተከሳሾቹ በተቀናጀ ሁኔታ የግል ተበዳዮችን በማታለል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተቀብለዋል።
ዋና ዋናዎቹ የክስ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡-
• የሀሰት ማንነት መፍጠር፦ 1ኛ ተከሳሽ (ዳዊት መንግስቱ) ራሱን ከመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳለው በመግለጽ፣ 2ኛ ተከሳሽን የከተማ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ባለሙያ፣ 3ኛ ተከሳሽን ደግሞ የቢሮ ኃላፊ ሹፌር አስመስለው በማቅረብ ተበዳዮችን አታልለዋል።
• የገንዘብ መጠኑ፦ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የሚገኝን 3,825 ካሬ ሜትር ይዞታ ወደ ዲጂታል ካርታ ለመቀየር በሚል ሂደት ውስጥ፣ የግል ተበዳይን በማታለል በአጠቃላይ 6 ሚሊየን 239 ሺህ 946 ብር በተለያዩ ጊዜያት እንዲከፍሉ አድርገዋል። ይህ ገንዘብ ለ4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች የባንክ ሂሳብ እንዲተላለፍ ተደርጓል።
• የሰነድ ማጭበርበር፦ ተከሳሾቹ “እንኳን ደስ አለህ ጉዳዩ ተጠናቋል” በሚል የአዲስ አበባ መሬትና ልማት ቢሮ ኃላፊን ሀሰተኛ ቲተር እና ክብ ማህተም በመጠቀም፣ የሀሰት የዲጂታል ካርታ ሰነድ ለተበዳዩ ሰጥተዋል።
•
በተጨማሪም 1ኛ ተከሳሽ ዳዊት መንግስቱ በሌላ ተበዳይ ላይ በፈጸመው መሰል ድርጊት ክስ ቀርቦበታል።
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 (ኮተቤ) አካባቢ የሚገኝን 49,500 ካሬ ሜትር የአርሶ አደር ይዞታ ወደ ዲጂታል ካርታ እቀይራለሁ በማለት 270 ሺህ ብር ተቀብሎ የሀሰት ሰነድ በመላክ ወንጀል መፈጸሙ በክሱ ተመላክቷል።
ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የማታለል ወንጀል፣ የመንግስት ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀትና በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል፣ በህገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ) በሚሉ የከባድ ሙስና ወንጀል ክሶችን መስርቶባቸዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት የክስ ዝርዝሩ ለተከሳሾች እንዲደርስ ያደረገ ሲሆን፣ ተከሳሾች ተዘጋጅተው ለመቅረብ በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ለመጋቢት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።