AMN -መጋቢት 18/2018ዓ.ም
የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ከድህነት ወለል በታች የነበሩ ዜጎችን የኑሮ መሰረት በመለወጥ በራስ አቅም የመቆም ግንዛቤን እያጎለበተ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ገለፁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዛሬዉ ዕለት በምግብ ዋስትና እና ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም 15 ሺህ 492 ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር አስመርቋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት በሶስት ዙሮች በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን በማፍራት ውጤት ማስመዝገቡን ኃላፊው ገልፀዋል።
የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ስራ ፕሮጀክት በመጀመሪያው ምዕራፍ 415 ሺህ 923፣ በሁለተኛው ምዕራፍ 107 ሺህ 398 ተጠቃሚዎችን በማቀፍ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎችን የኑሮ መሰረት መለወጥ መቻሉን ተናግረዋል።
ውጤቱ የተመዘገበው በእርዳታ ብቻ ሳይሆን በዜጎች ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት በራስ አቅም የመቆምን ግንዛቤ በማጎልበት ጭምር ነው ብለዋል።

ተመራቂ ወጣቶች በተለያዩ መስክ መሰልጠናቸውን ያነሱት አቶ ሚሊዮን፣ እራሳቸውንና ሀገራቸውን መጥቀም ወደሚችሉበት ደረጃ መሸጋገራቸውን ጠቁመዋል።
ተመሪቂዎቹ ከዚህ ቀደም የነበረባቸውን የተረጅነት እና የድህነት ቀንበር ሰብረው ዛሬ እራሳቸውን የሚግፉ፣ ወጪያቸውን መሸፈን ወደሚችሉበት እና ለሀገር ኩራት ወደሚሆኑበት አቅጣጫ ተሸጋግረዋል ብለዋል።
ተጠቃሚዎቹ በዘጠኝ ወራት ያገኙትን የስራ ልምምድ ወደ ስራ ላይ እንዲያውሉ ለማድረግ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የማስተሳሰር ስራ ስለመስራቱም ተገልጿል።
በታደሰ ሽፈራዉ