AMN- መጋቢት 19 /2018 ዓ.ም
የሁለት ልጆች እናት ለሆኑት ወይዘሮ ዘይነባ መሀመድ በአንድ ወቅት የቤት ኪራይ መክፈል ቀርቶ የዕለት ጉርስ ማግኘት አዳጋች የፈተና ጊዜ ነበር።
ዛሬ ግን ያ የተረጂነት ታሪክ ተቀይሮ በአዲስ ተስፋ ተተክቷል፤ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ህይወት ወጥተው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያልሙ ጠንካራ አምራች ለመሆን በቅተዋል።
ዜጎች የአካባቢያቸውን ፀጋ በመጠቀም ከተረጂነት በመላቀቅ ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩ የሚያደረጉ በርካታ ተግባራት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከተረጂነት ተነስተው ወደ ምርታማነት ከተሸጋገሩ ዜጎች መካከል ወ/ሮ ዘይነባ መሀመድ አንዷ ናቸው፡፡

ወ/ሮ ዘይነባ መሀመድ ሁለት ልጆችን ያለ አባት የሚያሳድጉ ሲሆን ቤተሰባቸውን ማስተዳደር አስቸጋሪ በመሆኑ ቀደም ሲል በከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ተጠቃሚ ነበሩ፡፡
በፕሮጀክቱ የነበራቸው ቆይታ ሲጠናቀቅ ክፍለ ከተማው ባዘጋጀው ዜጎችን ከተረጂነት የማላቀቅ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል።
እኔ እና ልጆቼ የቤት ኪራይ መክፈል እና የምንበላው እስከምናጣ ድረስ ተቸግረን ነበር ያሉት ወ/ሮ ዘይነባ አሁን ላይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት አማካኝነት በከተማ ግብርና 12 ሰዎች አንድ ላይ ተደራጅተው በከብት እርባታ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዜጎች ከተረጂነት በመላቀቅ ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ ምርታማ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ውጤታማ ክትትልና ድጋፎችንም እያከናወነ ሲሆን ፤ ዘመናዊ የሆነ የጤና ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው እና ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
መንግስት ባዘጋቸው መርሀ ግብር ተጠቃሚዎች ይህን ምቹ እድል ተጠቅመው ከብቶችን እያደለቡ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ነዋሪዎችን ከተረጂነት በማላቀቅ ምርታማ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራትን በትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ የትጽኅፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ አህመድ ኡርጎ ገልጸዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ