AMN — መጋቢት 19/2018 ዓ.ም
በዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችና የማጭበርበር ወንጀሎች አገራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ ከመጣላቸው በፊት፣ ተገቢውን የመከላከል ዝግጅት ማድረግና በቅንጅት መመከት እንደሚያስፈልግ የኢፌድሪ ፍትህ ሚኒስትር ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ ገለጹ።
ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደውና በዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ላይ በሚመክረው ሀገራዊ አውደጥናት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
ወ/ሮ ሀና በንግግራቸው የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር ክፍት መደረጉ፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት ማደጉ፣ የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ)፣ የመንግስት አገልግሎቶች እና እንደ ቴሌብር ያሉ የዲጂታል ፋይናንስ አማራጮች መበራከታቸው ለዘርፉ ዕድገት መሠረት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም “የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂን በስኬት በማጠናቀቅ ወደ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ራዕይ ለመሸጋገር የሚያስችል ጠንካራ አቅም መገንባቱን እንደሚያሳይ አብራርተዋል።
ይሁን እንጂ ከዘርፉ መስፋፋት ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣው የዲጂታል ፋይናንስ ማጭበርበር ይህንን ዓላማ እየተፈታተነው እንደሚገኝ ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው፣ የማጭበርበር ወንጀሉ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ይህ ወንጀል በተለይም በፋይናንስ ተቋማት፣ በንግዱ ማህበረሰብ፣ በግለሰቦችና በአጠቃላይ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ከመሆኑም ባለፈ በፖለቲካዊ መረጋጋትና በዜጎች ሥነ-ልቦና ላይም ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አስረድተዋል።
ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ ሥርዓት ለመገንባትም የፍትህ ተቋማት፣ የጸጥታና ደህንነት አካላት፣ የፌዴራልና የክልል የወንጀል ምርመራ ባለድርሻ አካላት፣ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች እንዲሁም ባንኮች እንደ አንድ አካል ሆነው በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሯ አሳስበዋል።
የአሁኑ የውይይት መድረክም ይህንን የትብብር ድልድይ ይበልጥ የሚያጠናክርና ለወደፊት የጋራ ስትራቴጂዎች መሠረት የሚጥል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በመድረኩ ላይ ከጸጥታና ደህንነት እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት የተወከሉ ከፍተኛ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
በታምሩ ደምሴ