AMN መጋቢት 19/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ አንጋፋውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፓርት ክለብ ከገጠመው የመፍረስ አደጋ ለመታደግ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገናል ብለዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግርኳስ ክለብ የተጫዋቹ እና የማህበሩ ብቻ ሳይሆን አንዱ የከተማችን ጠንካራ ክለብ ነው። በመሆኑም ይህንን አገራችንን እና ከተማችንን የወከለ ታሪካዊ የስፓርት ክለብ ከመፍረስ የመታደግ ኃላፊነት እንዳለብን እናምናለን።

ይህ አንጋፋ የስፓርት ክለብ ላለፋት 6 ወራት ደመወዝ መክፈል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ እና የመበተን አደጋ ተጋርጦበት ማየት ስለሌብን ከከተማችን በጀትም ወስነን፣ ለባለሀብቶች ባቀረብነው ጥያቄ መሰረት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ቢጂአይ ኢትዮጵያ በሰጡን ፈጣን ምላሽ በጥቅሉ የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለተቋቋመው ጊዜዊ ኮሚቴ አስረክበናል ብለዋል፡፡
ለከተማችን ወጣቶች፣ ለስፓርት ቢሮ እና ድጋፍ ላደረጉት ተቋማት በስፖርቱ ቤተሰብ ስም ከልብ አመሰግናለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህ ድጋፍ አስተዳደራችን ክለቡን ከውድቀት ለመታደግ እና ለስፓርት ወዳድ ህዝብ የሰጠው ክብር አንዱ ማሳያ ሲሆን፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉንም ባሳተፈ እና በግልፅነት አዲስ ቦርድ መርጦ ከገጠመው ጊዜያዊ ችግር ተላቆ ወደ ቀድሞ ጥንካሬውና ዝናው የሚመለስበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡