ተረጅነትን የረቱ እጆች

You are currently viewing ተረጅነትን የረቱ እጆች

ወይዘሮ እመቤት ሰለሞን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መሳለሚያ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ በምግብ ዋስትና (ሴፍቲኔት) መርሃ ግብር ታቅፈው ለሦስት ዓመታት ቆይተዋል፡፡ በክፍለ ከተማው ወረዳ 14 የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው መስራት ከጀመሩ ደግሞ ጥቂት ጊዜያት ሆኗቸዋል። ሥራ ሲጀምሩ ፕሮጀክቱ ከሚከፍላቸው ደመወዝ የሚቆጥቡትን እና ድጋፍ የተደረገላቸውን ገንዘብ ተጠቅመው የሴት ልብሶችን (ፒጃማ፣ ሻርፕ እና የውስጥ ልብሶችን) ሲሸጡ ነው ያገኘናቸው፡፡

በመርሃ ግብሩ ታቅፈው ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ልጆቻቸውን ለማሳደግ መስዋዕትነት እንደከፈሉ የተናገሩት ዓይናቸው በእንባ ተሞልቶ፣ ድምፃቸው ሲቃ እየተናነቀው ነው። “ባለቤቴ ተሯሩጦ ከሚሠራው የሚገኘው ገቢ ቤተሰብ ለማስተዳደር አያስችልም ነበር፡፡ ለልጆቼ ዳቦ መግዣ ሰው ቤት እንጀራ ጋግሬያለሁ፣ ጉሊት ጎመን ቸርችሬያለሁ፣ ባህላዊ ጌጣጌጦችን ሠርቼ ሸጫለሁ፤ የቻልኩትን ያህል ሥራ እሠራ ነበር፡፡ የማስበው ድሮ የመጣሁበትን የቤተሰቦቼን የተሻለ የሕይወት ታሪክ ሳይሆን፣ ልጆቼ የእኔን ዓይነት ኑሮ እንዳይኖሩና ተምረው ጥሩ ደረጃ እንዲደርሱ ነው” ሲሉ የቅርብ ጊዜ ትውስታቸውን ገለጹልን፡፡ ከነበረባቸው ኢኮኖሚያዊ ጫና በተጨማሪም ተሸክመው ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲንከራተቱ ወድቀው የዲስክ መንሸራተት አጋጥሟቸው እንደነበርም ነግረውናል፡፡

በምግብ ዋስትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጋቸው ያለፉትን ሕይወት “ነበር” ብለው እንዲያወሩ አድርጓቸዋል። በሴፍቲኔት ታቅፈው በየወሩ ከሚከፈላቸው ገንዘብ ከልጆቻቸው ጉሮሮ ቀንሰው የቻሉትን የሴቶች ልብሶችን በየቢሮውና በየመኖሪያ ቤቱ እየወሰዱ በሁለት ወር እንዲከፍሏቸው ይሸጡ ነበር፡፡ “በእጅ ሰጥቶ በእግር ልመና” እንዲሉ ብሩን ለመቀበልም ይቸገሩ ነበር፡፡ ከነበሩበት ውጣ ውረድ እና ችግር ለመውጣት የሚያስችላቸው መሸጫ ሱቅ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህን በተመለከተም፣ “ተሸክሜ ከመንከራተት ወጥቻለሁ፡፡ እረፍት በማግኘቴም ጤናዬ ተስተካክሎ በተሻለ ደረጃ ላይ እገኛለሁ፡፡ እንደበፊቱ ልጆቼን ምን እመግባቸዋለሁ ብዬ አልጨነቅም፡፡ በዕለት በማገኘው ገቢም ዳቦ ገዝቼ እገባለሁ፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ በዚህ ሱቅ ሠርቼ በቅርብ ጊዜ እለወጣለሁ፡፡ ከዝቅታ ከፍታም እንዳለ አምናለሁ” ሲሉ ያሉበትን ሁኔታና ተስፋቸውን ጭምር ነግረውናል፡፡

አቶ ሰለሞን ተስፋዬ በተመሳሳይ ከነበሩበት አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ መላቀቅ መቻላቸውን ያነሳሉ፡፡ “የምግብ ዋስትና (ሴፍቲኔት) ፕሮግራም ባለውለታዬ ነው” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡ ኑሮን ለማሸነፍና ስድስት ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር ጫማ ሥራ ተቀጥረው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም የሰቀቀን ኑሮ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በፕሮግራሙ መታቀፋቸው ከዚህ በፊት በሚሰጣቸው ብር ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር ችለዋል፡፡ አሁን ደግሞ የመሥሪያ ቦታ እና የድጋፍ አገልግሎት አግኝተው የግላቸውን “ሲቲና፣ ሰለሞንና ጓደኞቻቸው ቆዳና የቆዳ ውጤቶች የሽርክና ማህበር” በሚል ተደራጅተው እንዲሠሩ በተፈጠረላቸው ዕድል ጫማ፣ ቦርሳና ቀበቶ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ቀደም ሲል ጫማ ቤት ተቀጥረው ሲሠሩ በነበረበት ወቅትም በነፃነት ለመሥራት ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸው፣ “በአሁኑ ወቅት ቤት ኪራይ ሳልከፍል የራሴ የምለውን ሥራ በመሥራቴ ደስተኛ ነኝ፤ ራሴን እያሻሻልኩ እንድሄድም መንገድ ከፍቶልኛል” ይላሉ።

ተቀጥረው ይሠሩ በነበረበት ወቅት ስድስት ቤተሰብ ማስተዳደር ቀላል እንዳልነበረ የነገሩን አቶ ሰለሞን፤ ለግለሰብ ተቀጥረው ሲሠሩ በነበሩበት ጊዜ የነበረባቸው ጭንቀት ተወግዶ እፎይታን አግኝተዋል፡፡ ምንም እንኳን በሴፍቲኔት መሥሪያ ቦታ ተሰጥቷቸው ሥራ ከጀመሩ ጊዜው አጭር ቢሆንም ቤተሰቦቻቸውን እንዲመግቡ፣ የጀመሩትን ሥራ አስፋፍተው ወደፊትም የጫማ ፋብሪካ የመክፈት ሕልማቸውን እውን እንዲያደርጉ መነሻ እንደሆናቸው በደስታ ነግረውናል፡፡

“ማንኛውም ወጣት ዝቅ ብሎ በመሥራት ራሱን ከፍ አድርጎ ማሳየት መቻል አለበት” የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ሰዎች ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ተወካይና የሕብረተሰብ ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ አብርሃም እልፌ በከተማ ደረጃ ሴፍቲኔት መቼ እንደተጀመረ፣ የተቋቋመበት ዓላማ እንዲሁም ምን ያህል የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንዳደረገ የዝግጅት ክፍላችን አነጋግረናቸዋል፡፡

አቶ አብርሃም በሰጡት ምላሽ፤ መርሃ ግብሩ በ2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረ ሲሆን፤ ዓላማው በከተማዋ በዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ ዜጎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩና የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ማድረግ ነው፡፡ አለፍ ሲልም ሌሎችንም እንዲጠቅሙ ማስቻል ነው፡፡

በዚህ መሠረትም በዘንድሮው ዓመት ባለ አራት ወለል አራት ሕንፃዎች እና 19 ሼዶች ተገንብተዋል። በዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በመለየትም ተሰጥተዋል፤ ተጠቃሚዎቹም ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በባለ አራት ወለል አራት ሕንፃዎች ላይ 292 ኢንተርፕራይዞች እና 976 በቤተሰብ ተወካይ (አባወራዎችና እማወራዎች) እንዲሁም ከተገነቡት 19 ሼዶች ውስጥ ሁለቱ ሼዶች ለሌላ አገልግሎት የዋሉ ሲሆን፣ በ17 ሼዶች 17 ኢንተርፕራይዞች እና 170 በቤተሰብ ተወካይ ተሰማርተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በግንባታ፣ በከተማ ግብርና፣ በንግድ፣ በአገልግሎት ዘርፍ ሥልጠናዎችን እንደየዘርፋቸው የወሰዱ ናቸው፡፡

እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሦስት ዓመታት በፕሮግራሙ ታቅፈው የነበሩና በኮሚቴ በመለየት፣ በሕብረተሰቡ በመተቸት፣ በቅሬታ ኮሚቴ ታይተው የተመረጡ ናቸው፡፡ ከዚያም ለእያንዳንዳቸው 600 ዶላር የማቋቋሚያ ድጋፍ ተደርጎላቸው ከተረጂነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ የተደረጉ ናቸው።

እነዚህ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች በአስቸጋሪ ሕይወትና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩ ናቸው የሚሉት አቶ አብርሃም፤ ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸው የነበረባቸውን ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ጫና በመቅረፍ የ“ይቻላል” መንፈስ እንዲላበሱ ያደርጋቸዋል። ከኢኮኖሚ አንፃር ከሌሎች ሲጠብቁ የነበረውን ራሳቸውን እንዲችሉ ያግዛቸዋል፡፡ ራሳቸው ተለውጠው ለሌሎችም የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል፡፡ እስካሁን በተሠሩት ሥራዎችም እነዚህን ለውጦች አምጥተው ተመልክተናል፡፡

መርሃ ግብሩ በከተማ ደረጃ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ቀጥታ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ የተለያዩ የድጋፍ ሥራዎች ላይ ነው። የአመለካከት፣ የሕይወት ክህሎት እና ሙያዊ የሆነ ቴክኒካል ሥልጠናዎች ይሰጧቸዋል፡፡ በባለሙያ የተደገፈ የምክር አገልግሎት እንዲያገኙም ይደረጋል። በዋናነትም ትኩረት የሚደረገው በዘላቂነት ኑሯቸውን በሚለውጡ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ነው፡፡

“በቅርብ ጊዜ የሥራ ዕድል ተመቻችቶላቸው ወደ ሥራ የገቡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ምርታማ መሆናቸው ብቻ በቂ አይደለም” ያሉት አቶ አብርሃም፤ ለምሳሌ እንቁላል ማምረት የጀመሩትን ከሆቴሎችና ነጋዴዎች ጋር ትስስር የመፍጠር፣ ሥራቸውን ይዘው እንዲወጡ ባዛር ማዘጋጀት፣ ለእነሱም ቅድሚያ መስጠት፣ የተለያዩ ባለሃብቶችን በማነጋገርና ከማይክሮ ፋይናንስ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የማመቻቸት፣ ብድር ከወሰዱም በኋላ ከገንዘብ አያያዝ እና ተግባብቶ መስራት እንዲችሉ ሥልጠና የመስጠት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡

ከግብር ጋር ተያይዞ ስምምነት ሲያደርጉ የእፎይታ ጊዜ እንዲያገኙ ውል እንዳይዋዋሉ የማቆየት ሥራ በመሥራትም ትልቅ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡

በምግብ ዋስትና (ሴፍቲኔት) መርሃ ግብር ታቅፈው ወደ ሥራ የገቡ ዜጎች የወደፊት ሕልማቸውን ለማሳካት በር ከፍቶላቸዋል፡፡ “አይቻልም” የሚለውን መንፈስ እንደሚቻል ማሳየት ችለዋል። ሁልጊዜ ተረጂ ነን ከሚል አስተሳሰብና ትናንት ከነበሩበት ችግር ወጥተው መስራት እንደሚችሉና አቅም እንዳላቸው ተረድተውበታል፡፡ መስራት መሻገር እንደሆነና ወደፊትም የተሻለ ሕይወት እንደሚኖሩ መሠረት የሚሆናቸው ነው፡፡ ይህ ሲሆን ከራሳቸው አልፈው ሀገራቸውንም ጭምር የሚጠቅሙ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

በከተማዋ እየተተገበሩ ካሉ የዜሮ ግብ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ተረጂነት እና ልመናን ዜሮ ማድረግ ነው። ለዚህም በዘንድሮው የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ላይ በአዲስ ከተማ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በየካ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች፣ አራት ባለ አራት ወለል የማምረቻ እና መሸጫ ሕንፃዎችን ከዚህ ቀደም በምግብ ዋስትና (ሴፍቲኔት) ፕሮግራም ታቅፈው ሲሠሩ ለነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በማስረከብ ወደ ሥራ መግባታቸው የሚታወስ ነው፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review