“ከዚህ በፊት ቅሬታችንን አሰምተናል፤ ነገር ግን ዘላቂ መፍትሄ አልተሰጠንም”
በቦሌ አራብሳ ሰፈራ የሚኖሩ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ሰራተኞች
“ችግሩን ለመፍታት እየሰራሁ ነው”
የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት
ወይዘሮ አየለች ጎዳ ቦሌ አራብሳ ሰፈራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሳይት አምስት ነዋሪ ናቸው፡፡ ጠዋት ከቦሌ አራብሳ ወደ ፒያሳ ማታ ደግሞ ከፒያሳ ቦሌ አራብሳ መጓጓዝ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነው። በየእለቱ እንዲመላለሱ ያስገደዳቸው ህይወታቸውን የሚመሩበት ስራቸው ሲሆን የሚመላለሱትም ለመንግስት ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ በተመደቡት አውቶብሶች ነው፡፡ “ይህ መሆኑ እኔን ጨምሮ የመንግስት ሰራተኛው በሰዓቱ ስራ ቦታ ደርሶ በአግባቡ እንዲያገለግል ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ታክሲ ጋር በመሰለፍ የሚያጠፋውን ጊዜና ገንዘብም ታድጎለታል” ሲሉ ፋይዳውን ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ አየለች አገልግሎቱ እጥረት እንዳለበት አልሸሸጉም፡፡ “ወንበር ሳይሆን መቆሚያ ቦታ ለማግኘት ከቤቴ 11፡00 ሰዓት እወጣለሁ፡፡ ለ2፡00 ሰዓት ያህልም እቆማለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት ወገቤን እና እግሬን ያመኛል፡፡ በስራ ቦታም በጠዋት ስለሚደክመኝ ስራዬን ደስተኛ ሆኜ ለመስራት እቸገራለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የስራ ባልደረቦቼ በሌሊት ሲወጡ የድብደባ ወንጀል ደርሶባቸው ተመልክቻለሁ” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
“የጠዋት መቆሜ ማታም እንዳይደገም ከስራ ሰዓት ቀደም ብዬ እወጣለሁ” የሚሉት ወይዘሮ አየለች፤ ለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በዚህ መስመር ስላለው የመንግስት ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ሀሳባቸውን ያጋሩን ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በተገልጋዮቹ ተመርጠው የማስተባበር ስራ እየሰሩ የሚገኙት ኮሎኔል ደምሴ ተሰማ ናቸው። በአስተያየታቸውም፣ “የምንሳፈርበት አውቶቡስ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት በሚሰለፉ ተገልጋዮች ይሞላል፡፡ እነዚህ አካላት ሌሊት ወጥተን አንነሳም በሚሉበት ወቅት ህፃናት የያዙ፣ ነፍሰጡር እናቶች እና አቅመ ደካሞችም ጭምር ወንበር እንዲያገኙ ለማድረግ ያለው ፈተና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ተገልጋዩ ረጅም ሰዓት ከመቆሙ የተነሳ ለጤናም ችግር እየሆነበት ነው፡፡ ይህ ችግር ይፈታልን ዘንድ ከዚህ በፊት ቅሬታችንን አሰምተናል፤ ነገር ግን ዘላቂ መፍትሄ አልተሰጠንም” ብለዋል፡፡
“ነፍሰጡር ሆኜ፣ ህፃን ይዤ ወይም አቅመ ደካማ ሆኜ ስለማያዩኝ ሰዎች አይረዱኝም፡፡ የውስጤን ህመም እኔና ፈጣሪ ብቻ ነን የምናውቀው፡፡ አንዱ ኩላሊቴ ፌል አድርጎ ቀሪው አንዱም ግማሽ ክፍሉ ተጎድቷል ተብዬ በግማሽ ኩላሊት ነው የምኖረው፡፡ በዚሁ ላይ መቆም ሲጨመርበት ምን ያህል ሊያባብሰው እንደሚችል መገመት አያዳግትም” የሚሉት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ስማቸው ለዚህ ፅሁፍ ሲባል የተቀየረ ወይዘሮ ሰላም አንዳርጌ ናቸው፡፡
“ይህንን ችግሬን ተረድቼ መነሻውን ቦሌ አራብሳ አድርጎ እስከ ፒያሳ የሚወስደውን አውቶቡስ ለመያዝ 11፡00 ሰዓት ከቤቴ እወጣለሁ፡፡ እንደዚህም ሆኖ ወንበር የማላገኝባቸው ቀናት ብዙ ናቸው፡፡ ህፃናቱም አየር ሲያጥራቸው ያለቅሳሉ” የሚሉት ወይዘሮዋ፣ ይህ የሆነው በቂ አውቶቡስ ባለመኖሩ ምክንያት እንደሆነና የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በዚህ መስመር ከወራት በፊት በሰራው ዘገባ መሰል ችግሮች እንደነበሩ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ስለዚህ በዚህ ልክ እየተነሳ ላለው ጉዳይ እና በሌሎች ረጅም ርቀት ባለባቸው አካባቢዎች ያለውን መሰል ችግር ለመፍታት ምን እየተሰራ እንደሆነ መልስና ማብራሪያ እንዲሰጡን በፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ቤዛዊት ተሾመን ጠይቋል፡፡
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ የመንግስት ሰራተኛው በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት አገልግሎት የሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት ከተጀመረ 11 ዓመት ሆኖታል፡፡ ይህም ሰራተኛው በሰዓቱ ተገኝቶ ስራውን በአግባቡ እንዲሰራ በማድረጉ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡
አገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ ከማድረግ እና እጥረቱን ከመቅረፍ አንፃር አሁንም የሚነሱ ቅሬታዎች እንዳሉ ያልሸሸጉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ የመንግስት ሠራተኛው ከጊዜ ወደ ጊዜ የሥራና የመኖሪያ ቦታ ይቀያይራል። ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሰራተኛ በማስፋፊያ አካባቢዎች ይኖራል። ይህንን ችግር በጊዜያዊነት ለመፍታት መስመሮችን የመጨመር እንዲሁም የማራዘም ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
ይህም ማለት የሰው ብዛቱ አነስ ያለባቸው ቦታዎች ላይ ሁለት አውቶቡሶች ካሉ አንዱን ብቻ እንዲጠቀሙ በማድረግና አንዱን ደግሞ እጥረት ባለባቸው ቦታዎች አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በዚህም ለምሳሌ፡- ኮዬ ፈቼ ከ20 አውቶቡሶች ወደ 35 ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡
ሌላኛው በጊዜያዊነት እንደመፍትሄ የተወሰደው 17 የሚሆኑ ሃገር አቋራጭ አውቶቡሶች ለሰራተኛው አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በየቅርንጫፉ ተጠባባቂ ተብለው የሚቀመጡ ከሁለት እስከ አራት አውቶብሶችም ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡
ሰዎች በብዛት የሚኖሩበትን ቦታ ያማከለ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቅረብ በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የሙሉ መስመሮች መረጃ በጂ አይ ኤስ ተይዞ ጥናት እየተደረገበት ይገኛል፡፡
“ሌላኛው በፐብሊክ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያለውን እጥረት በቋሚነት የሚፈታው አውቶቡሶችን ገዝቶ ማስገባት ነው፡፡ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ከዚህ በፊት 90 ፐብሊክ ሰርቪሶችን ለመግዛት ዓለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ ወጥቶ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በሚወስድ ገንዘብ ግዢ ለመፈጸም ውል መገባቱ ይታወሳል፡፡” የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ ነገር ግን ከባንክ ብድር ማግኘት ስላልተቻለ ግዥው ሳይፈፀም መቆየቱንና በአሁኑ ወቅት ሌሎች የፕሮጀክት ስራዎችን በማቆም የአውቶቡስ ግዥው እንዲካሄድ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
መኪናዎቹ ብዙ ዓመት አገልግሎት ከመስጠታቸው ጋር ተያይዞ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን በማስጠገን ቶሎ ወደ ስራ እንዲገቡም እየተደረገ ይገኛል። እንዲህም ተደርጎ አሁንም ድረስ ቅሬታዎች እየቀረቡ መሆኑን እና ተቋሙ መፍትሔ ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ