AMN መጋቢት 19/ 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ጎልፍ አሶሴሽን ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው የሴቶች የጎልፍ ውድድር በአረንጓዴው ሜዳ ተካሂዷል፡፡
ውድድሩ ስፖርታዊ ፉክክር ብቻ ሳይሆን የሴቶችን ጥንካሬ፣ ስልጣኔ እና አዲስ ራዕይን ያሳየ መድረክ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከልዩ ልዩ የሀገር ውስጥ ተቋማትና ከዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የተውጣጡ በአምስት ምድቦች ተከፋፍለው ወደ ሜዳ የገቡት 16 ምርጥ ሴት ተወዳዳሪዎች እንደሆኑም ተመላክቷል።
በዚህ መድረክ ብርቱ ፉክክር በማድረግ የጽናት ተምሳሌት ሆነው የታዩት የመከላከያ ቅርስና ሙዚየም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ጥሩዬ አሰፌ ስፖርቱ ለጤና ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ትልቅ የገቢ ምንጭ መሆን የሚችል ዘርፍ ነው ብለዋል።
ስፖርቱ በሰዎች መካከል ያለውን ዝምድና የሚያጠናክር የዲፕሎማሲ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን አንስተዋል።
በሀገሪቱ ብቸኛውና ደረጃውን የጠበቀ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳ በመከላከያ ተቋም ውስጥ መገኘቱ ደግሞ ተቋሙ ለስፖርቱ እድገትና ለጤናማ ማህበረሰብ ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የጎልፍ ክለቡ ለሁሉም ክፍት መሆኑን ያስታወሱት ጀነራል መኮንኗ ተቋሙ ባመቻቸው በዚህ ዕድል በመጠቀም ሁሉም ስፖርቱን የህይወቱ አካል እንዲያደርገው ጥሪ ማስተላለፋቸዉን ኤኤምኤን ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ኦንላይን ሚዲያ ያገኘዉ መረጃ ያመላክታል፡፡