ሉዓላዊነት ማለት ዳር ድንበርን ከመጠበቅ ባሻገር፣ የዜጎችን አንገት የሚያስደፋውን የልመና እጅ ሰብሮ በራስ ምርት መቆም ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመሰገን ጥሩነህ

You are currently viewing ሉዓላዊነት ማለት ዳር ድንበርን ከመጠበቅ ባሻገር፣ የዜጎችን አንገት የሚያስደፋውን የልመና እጅ ሰብሮ በራስ ምርት መቆም ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመሰገን ጥሩነህ

AMN — መጋቢት 19/2018 ዓ.ም

የአፋር ሕዝብ ለዘመናት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በንቃትና በጀግንነት ሲጠብቅ የኖረ የቁርጥ ቀን የሀገር ባለውለታ ነው። ዛሬ ደግሞ በረሃውን በማለምለምና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ጥንካሬ በመገንባት አለኝታነቱን ዳግም እያደሰ ይገኛል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመሰገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ባሰፈሩት መልእክት ገልፀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፋር ምድር መርቀን ለአገልግሎት ያበቃነው የተንዳሆ መስኖ ልማት የማጠናቀቂያ እና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክት፣ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ትግላችን የድል ዓርማ ነው ብለዋል ።

ለዓመታት ተጓትቶ፣ ተስፋ አስቆርጦና የጎርፍ ሥጋት ሆኖ የቆየውን ግድብ፣ በቆራጥ አመራርና በፈጣን አፈጻጸም ወደ ልማት አውታር ቀይረነዋል። ይህ ፕሮጀክት ለምድራችን በረከት፣ ለሕዝባችን የብልጽግና ምንጭ እንዲሆን ዳግም ተወልዷል ።

እውነተኛ ነጻነትና ምሉዕ ክብር የሚረጋገጠው በራስ ማሳ ላይ በሚለማ ሰብል፣ በራስ ጉልበት በሚገራ ውኃና ከማንም እጅ በማይጠበቅ የዜጎች የዕለት ጉርስ ነው። የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተነሣነውም የዜጋን ክብርና የሀገርን የህልውና መሠረት ለማጽናት ነው ።

የዚህ ዋናዎቹ ዐቅሞቻችን ደግሞ ያልተነካው የበረሃ ለም አፈራችን፣ ውኃችን፣ ትጉህ ሕዝባችንና የመስኖ አውታሮቻችን ናቸው። ለእኛ መስኖ ማለት የዝናብ ጠባቂነትን ታሪክ መዝጋት ነው፤ መስኖ ተለዋዋጭ የሆነውን የዓለም ጂኦ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥረት የምንቋቋምበት ብቸኛውና አስተማማኙ መከታችን ነው ።

የቆላማ አካባቢዎቻችንን እምቅ ሀብት ማልማትና የዜጎቻችንን ሕይወት በዘመናዊ የኮሪደር ልማት ማሣለጥ የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን የመወሰን ጉዳይ መሆኑን ምከትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመሰገን ጥሩነህ ቃልን በተግባር፣ ሐሳብን በውጤት እየለወጥን፣ አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩንና ባለ ሀብቱን ያስተሣሠረ የልማት ሠንሰለት በመፍጠር፣ ኢትዮጵያን በምግብ ራሷን የቻለች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የምትተርፍ የብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋታለን ብለዋል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review