AMN -መጋቢት 20 /2018 ዓ.ም
በሕክምናው ዓለም ዲሜንሺያ እየተባለ የሚጠራው የመርሳት ችግር ፣ አንድ ሰው በቀን ተቀን እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር የማስታወስ፣ የማሰብ፣ ነገሮችን የመረዳት ወይም ደግሞ የመመራመር ብቃቱ ሲቀንስ የሚገለፅበት ስያሜ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የነርቭ ሀኪም እና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ያሬድ ዘነበ ለኤ ኤም ኤን እንደ ገለጹት፣ የመርሳት ችግር ከ65 ዓመት በላይ ባሉ ሰዎች ላይ በብዛት ይታያል።
እርጅና በራሱ የመርሳት በሽታ ባይሆንም፣ ዕድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ግን ለዚህ ችግር የመጋለጥ ዕድል እየሰፋ ይሄዳል።

ከመርሳት በሽታ አይነቶች ውስጥ በብዛት የምናገኘው የአልዛይመር ህመም ነው። ከዚ በመቀጠል ደግሞ ከደም ዝውውር ጋር የተያያዙ፣ ለምሳሌ በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ ወይም የደም መርጋት (Stroke) ካጋጠመ በኋላ የሚመጣ የመርሳት ችግር ሊኖር ይችላል።
በአልዛይመር ጊዜ በጭንቅላታችን ውስጥ ያሉ የነርቭ ሴሎች መሞት ይጀምራሉ።
በተለይም ደግሞ ለመረጃ መቀበያ እና ለማስታወሻነት የሚያገለግለው የጭንቅላታችን ክፍል ሂፖካምፐስ የምንለው ክፍል መኮማተር ወይም መጠኑ መቀነስ እንደሚጀምር ነው የነርቭ ሀኪም ዶክተር ያሬድ ዘነበ የሚገልፁት።
በዚህ ሳቢያ በነርቭ ሴሎች መካከል ያለው መረጃ የመለዋወጥ ሂደት እንደሚቋረጥ አስረድተዋል።
ዋና ዋና ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
የቅርብ ጊዜ ትውስታዎችን መርሳት፦ ለምሳሌ ያደረጉትን ነገር፣ የበሉትን ምግብ ወይም የሄዱበትን ቦታ ወዲያውኑ መርሳት ይስተዋላል።

ነገሮችን የማከናወን ችግር፦ ቀለል ያሉ የቤት ውስጥ ስራዎችን፣ ለምሳሌ ምግብ ማብሰል ወይም ልብስ መልበስ ሊከብዳቸው ይችላል።
የመግባባት ችግር፦ ትክክለኛውን ቃል ፈልጎ ለማግኘት መቸገር ይከሰታል።
የባህሪ መለወጥ፦ መነጫነጭ፣ ድብርት ወይም ደግሞ ያለምክንያት መፍራት ይስተዋልባቸዋል።
ምን ጥንቃቄዎች ይደረጉ?
የመርሳት በሽታን ሙሉ በሙሉ መፈወስ ባይቻልም፣ አስቀድሞ በመመርመር ግን ህመሙ እንዳይባባስ ማድረግ እንደሚቻል ነው ዶክተር ያሬድ ዘነበ የጠቆሙት።
ጤናማ አመጋገብ መከተል፣የደም ግፊትን እና ስኳርን መቆጣጠር፣ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ አእምሮን የሚያሰሩ ስራዎችን (ለምሳሌ ንባብ) ማዘውተር ተገቢ እንደሆነ የነርቭ ሀኪሙ ዶክተር ያሬድ ዘነበ መክረዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ