AMN -መጋቢት 21/2018 ዓ/ም
አዲስ አበባ ለዘመናት የቆዩትንና በካይ ጋዝ የሚተነፍሱ ሞተሮችን ጩኸት፣ በዘመናዊ የኤሌክትሪክ ባትሪዎች ድምፅ አልባና ቀልጣፋ እንቅስቃሴ እየተካች ትገኛለች።
መዲናዋ ቀደም ሲል በታወቁት ሰማያዊና ነጭ ሚኒባስ ታክሲዎችዋ ብትታወቅም፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረትን የሳበ የታሪካዊ አረንጓዴ የትራንስፖርት ሽግግር ማዕከል ሆናለች።
ብዙ ሀገራት የሽግግር ጊዜ ገደባቸውን እስከ 2030ዎቹ እያሰሉ ባሉበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2024 አዳዲስ የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ በመከልከል በዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር የሚያደርጋትን ደፋር እርምጃ ወስዳለች።
ይህ ውሳኔ በቅርቡ ሁሉንም የነዳጅ ተሽከርካሪ መለዋወጫዎችንና የጭነት መኪናዎችን እስከማካተት ደርሷል። ይህ ፖሊሲ በደማቋ አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የሚታይ ፍሬ እያፈራ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ነዳጅን ቀድማ የገፋችበት ምክንያት በድንገት በመጣ የአካባቢ ጥበቃ ፍቅር ብቻ አይደለም፤ ከበስተጀርባው ጠንካራና ተግባራዊ የሆነ የኢኮኖሚ ስሌት እንጂ።
ሀገሪቱ በየዓመቱ ለነዳጅ ግዥ ከ4.5 ቢሊዮን እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች። ይህም የሀገሪቱን ውስን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ክፉኛ ሲፈታተነው ቆይቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ርካሽና የተትረፈረፈ የታዳሽ ኃይል ሀብት አላት።
ግዙፉን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ፣ ሀገሪቱ አብዛኛውን የኤሌክትሪክ ኃይል የምታመነጨው ከንጹህ የውሃ ኃይል ነው።
በኢትዮጵያ መኪናን በኤሌክትሪክ ማንቀሳቀስ ከነዳጅ ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ ታሪፍም ከሌሎች ሀገራት አንጻር እጅግ ዝቅተኛ የሚባል ነው።
በእነዚህ ምክንያቶች ሽግግሩ እጅግ ፈጣን ሆኗል። በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ድርሻ ከጠቅላላው ተሽከርካሪ ክምችት ከ1% በታች የነበረው፣ አሁን ወደ 6% እና 8.3% ከፍ ብሏል። ይህም ከዓለም አቀፉ አማካይ የሽግግር ፍጥነት በእጅጉ የላቀ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አውቶብሶችን በልዩ የትራንስፖርት መስመሮች ላይ ያሰማራ ሲሆን፣ ይህም ለመንገደኞች ከበካይ ጋዝ የጸዳና ፈጣን ጉዞን እየሰጠ ይገኛል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. እስከ 2032 ድረስ ግማሽ ሚሊዮን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በጎዳናዎች ላይ ለማሰማራት አልማ እየሰራች ሲሆን፣ ለዚህ ስኬትም ሰፊ የታክስ ማበረታቻዎችን እያደረገች ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ ብስክሌትን እንደ አማራጭ መጠቀም የሚያስችልና ለእግረኞች ምቹ የሆኑ መንገዶችን በስፋት አካቷል። እርግጥ ነው፣ ያለምንም ተግዳሮት የሚመጣ አብዮት የለም። በማደግ ላይ ባለ ሀገር ውስጥ ይህን ግዙፍ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ማስተናገድ የራሱ ፈተናዎች አሉት። የቻርጅ ማደያዎች እጥረትና የመሠረተ ልማት በበቂ ሁኔታ አለመሟላት የታዩ ቢሆንም፣ ዘርፉን ከዕድገት አልገደቡትም።
በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ግጭት የዓለምን የነዳጅ አቅርቦት በሰጋበትና የበለፀጉ ሀገራት ሳይቀር በነዳጅ ቀውስ በሚፈተኑበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ የቀደመ የታዳሽ ኃይል እርምጃ የፖሊሲውን ትክክለኛነት የማያሻማ አድርጎታል። አዲስ አበባ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ለአረንጓዴ ሽግግር ምዕራባውያንን ብቻ መጠበቅ እንደሌለባቸው በተግባር እያሳየች ነው።
የትራንስፖርት ስልቷን ከሀገር ውስጥ የታዳሽ ኃይል ምርት ጋር በማስተሳሰር፣ መላው አፍሪካና የተቀረው ዓለም በቅርበት የሚከታተሉትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየጻፈች ትገኛለች።
በይታያል አጥናፉ