AMN- መጋቢት 21/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ የባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች መልቲ-ኤቨንት ፌስቲቫል ለማዘጋጀት ተመርጣለች።
የአፍሪካ ባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን (ATSGC) በቅርቡ የአባልነት ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን (ECSF) ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ታሪካዊ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነትም በይፋ ተፈራርሟል።
ይህ ስምምነት በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ሲሆን በተለይም የአፍሪካን ሀገር በቀል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስተዋወቅ እንዲሁም ተደራሽነታቸውን ለማስፋት ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑ ተገልጿል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በአህጉራዊው ኮንፌዴሬሽን ውስጥ ያላትን ተሳትፎ የሚያጠናክር እና የአፍሪካን ባህላዊ እሴቶች በስፖርት አማካኝነት ለማስተሳሰር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ መኪዩ መሀመድ “ስምምነቱ ኢትዮጵያ ያላትን ጥንታዊ እና ደማቅ የባህል ስፖርት እሴቶች ከአህጉራዊው እንቅስቃሴ ጋር ለማስተሳሰር የሚረዳ ትልቅ ምዕራፍ ነው ያሉ ሲሆን መንግስት ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ በመስራት የሀገር በቀል ስፖርቶች እንዲያድጉ እና ለትውልድ እንዲተላለፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል” ብለዋል።
ከፊርማ ስነስርዓቱ በኋላ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሕይወት መሀመድ በበኩላቸው ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች አዲስ ምዕራፍ መሆኑን አመላክተዋል።
የኮንፌዴሬሽኑ ሊቀመንበር ዶ/ር ኪይካማቱዋ በበኩላቸው “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ባህል እና ታሪክ መገኛ በመሆኗ ይህንን ታሪካዊ ክስተት ለማስተናገድ የተመረጠችበት ምክንያት አሳማኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ሁለቱ ተቋማት በቴክኒክ ድጋፍ፣ በሚዲያ አጠቃቀም፣ በባህላዊ ጨዋታዎች ሕግጋት ዝግጅት እና በስልጠና ዙሪያ በቅርበት እንደሚሰሩ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን አስታውቋል።