AMN — መጋቢት 21/2018 ዓ.ም
በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተዉ ቀውስ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም፣ መንግስት የተለያዩ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡
መንግስት የነዳጅ ግብይት እና ስርጭትን ለማሻሻል ቀደም ብሎ የጀመራቸው የማስተካከያ እርምጃዎች አሁን ያለዉን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ለመቋቋም እያገለገሉ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፣ መንግስት ለነዳጅ ግዢ በየዓመቱ ከ4.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ይመድባል። ይህ ከፍተኛ ሃብት የሚፈስበት ዘርፍ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልና በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዳይወጣ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል።
ከድጎማ ጋር በተያያዘም መንግስት ሲከተለው የነበረውን አጠቃላይ ድጎማ ደረጃ በደረጃ የማንሳት ፖሊሲ ተግባራዊ እያደረገ ሲሆን፣ ይህም የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መናርን እና የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ማሻሻያን ታሳቢ ያደረገ የችርቻሮ ዋጋ ማስተካከያ እንዲደረግ አስገድዷል። በተለይም ለህዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ የሚሰጠው የታለመ ድጎማ በሂደት እየተቀነሰ እንዲቀር እየተሰራ ይገኛል። የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዘርፉ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችን ለመሙላት ቴክኖሎጂን በስፋት ስራ ላይ አውሏል።
በአሁኑ ወቅት በማንኛውም የነዳጅ ማደያ የሚፈጸሙ ግብይቶች በዲጂታል መንገድ ብቻ እንዲከናወኑ በመደረጉ፣ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ከመቀነስ ባለፈ የእያንዳንዱን ማደያ እና ተሽከርካሪ የነዳጅ ስርጭት እንቅስቃሴ በቀላሉ ለመከታተል ተችሏል።

ከዚህም በተጨማሪ የነዳጅ ቦቴዎች ከተመደበላቸው መስመር እንዳይወጡና ለኮንትሮባንድ እንዳይጋለጡ በሳተላይት የታገዘ የክትትል ስርዓት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
ከቁጥጥር እርምጃዎች ጋር በተያያዘም ነዳጅ ደብቀው በሚገኙ ወይም ያለአግባብ በሚያከፋፍሉ ማደያዎች ላይ የፈቃድ ስረዛና የቋሚ እገዳ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። እንዲሁም ልዩ ፈቃድ ካላቸው የልማት ስራዎች ውጭ በጀሪካንም ሆነ በሌሎች መያዣዎች ነዳጅ መቅዳት ሙሉ በሙሉ ተከልክሏል።
የአቅርቦት መቆራረጥ እንዳይከሰትም በተለይ በጅቡቲ በኩል የሚገባው ነዳጅ በወቅቱና በፈጣን ሁኔታ እንዲጓጓዝ ቅድሚያ ተሰጥቶታል። የሀገሪቱን የነዳጅ ክምችት አቅም ለማሳደግም አዳዲስ ዲፖዎችን የመገንባት እና ነባሮቹን የማስፋፋት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ መንግስት ነዳጅ ከሚገዛበት ዓለም አቀፍ ዋጋ አንጻር ሲታይ የሀገር ውስጥ መሸጫ ዋጋው አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚቀርበው ነዳጅ በተቀመጠለት የዋጋ ተመንና የግብይት ሰንሰለት እንዳይሸጥ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን በጥናት መረጋገጡን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በመሆኑም በመካከለኛው ምስራቅ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የአቅርቦት መስተጓጎል እንዳይፈጠር መንግስት አማራጭ መንገዶችን እየተጠቀመ መሆኑንና በህገ-ወጥ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሃገሪቱን ነዳጅን በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችሉ የአሰራር ስርዓቶችም በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ