የነገው መሠረት ዛሬ ነው፤ በጊዜ አትደራደሩ- ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ

You are currently viewing የነገው መሠረት ዛሬ ነው፤ በጊዜ አትደራደሩ- ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ

AMN- መጋቢት 21/2018 ዓ.ም

በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ በገንዘብ ሊተካ የማይችል ብቸኛው ሀብት ጊዜ ነው፣ አብዛኞቻችን ለስኬታማነታችን ማነስ እንደ ምክንያት የምናቀርባቸው ክህሎት፣ ዕድል ወይም የገንዘብ አቅም ሊሆኑ ይችላሉ።

ሆኖም ግን፣ የዓለማችን ስኬታማ ሰዎች ታሪክ ሲመረመር ልዩነቱ የሚመነጨው ካላቸው ችሎታ ሳይሆን፣ቁልፉ ያለው ለሁላችንም እኩል የተሰጠንን 24 ሰዓት የምንጠቀምበት መንገድ መሆኑን ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ይናገራል።

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ የሥራና የሕይወት ተሞክሮውንና ልምዱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተገኝቶ ለተማሪዎችና ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አካፍሏል።

በተለያዩ አጋጣሚዎች ሁሌም እንደሚያሳስበው፣ ጊዜ ለድሃውም ለሀብታሙም፣ ለተማረውም ላልተማረውም እኩል የተሰጠ ፀጋ ነው ይላል።

ልዩነቱ የሚፈጠረው ግን ይህንን ውድ ስጦታ በአግባቡ መጠቀም በሚችሉትና በሚያባክኑት መካከል መሆኑን በግልፅ ለታዳሚያኑ አብራርቷል።

ጊዜውን በአግባቡ የሚጠቀም ሰው ወደ ስኬት ማማ ላይ ሲወጣ፣ ጊዜውን ያለ እቅድ የሚያሳልፍ ግን የኋላ ቀርነት ሰለባ መሆኑ የማይቀር ሃቅ መሆኑንም ያነሳል።

ለኃይሌ ጊዜ ማለት ዝም ብሎ የሚያልፍ ሰዓት ሳይሆን፣ የድልና የሽንፈት መለያ መስመር ነው።

አትሌቱ በሩጫ ታሪኩ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ልዩነት የወርቅ ሜዳሊያ ሲያሸንፍ፣ ሌላው ተፎካካሪው በዚሁ ቅጽበት ሳይሳካለት በመቅረቱ የሚፈጠረውን የድል ስሜት ምን ያህል ውድ እንደሆነም አብራርቷል።

ይህ ተሞክሮ የሚያስተምረን እያንዳንዷ ሴኮንድ በሕይወታችን ውስጥ ምን ያህል ትልቅ ዋጋ እንዳላት፣ ዛሬ የምናባክናት አንዲት ደቂቃ፣ ነገ ለምንፈልገው ትልቅ ግብ እንቅፋት ልትሆን እንደምትችል ነው በማለት የጊዜን ውድነት አስገንዝቧል።

የነገው መሠረት ዛሬ ነው፤ በጊዜ አትደራደሩ” የሚለው የኃይሌ መርህ፣ ዛሬ የምናደርጋቸው ትናንሽ ተግባራት የነገው ማንነታችን መሠረቶች መሆናቸውን ያሳየናል።

ስኬት በአንድ ጀምበር የሚመጣ ሳይሆን፣ በየቀኑ በምናደርገው ጥንቃቄ የተሞላበት የጊዜ አጠቃቀም የሚገነባ ውጤት መሆኑን ሁሉም ልብ ሊለው የሚገባ የዕለት ተዕለት ተግባር መሆኑንም መረዳት አለብትም ይላል።

በሕይወት ጉዞ ውስጥ ውድቀት ሊያጋጥም ይችላል፣ ዋናው ቁምነገር ግን ከወደቅንበት ተነስተን፣ ከስህታችንት ተምረን ጊዜን እንደገና አደራጅቶ ጥረትን መቀጠል ላይ ነው።

አትሌት ኃይሌ እንደሚለው “ራስህን ሁን፣ ጠንክረህ ሥራ፣ ጊዜህንም በአግባቡ ተጠቀም፤ ያኔ ስኬት ደጅህ ይቆማል።”

በጥቅሉ ስኬት የሩቅ ምስጢር ሳይሆን በእጃችን ያለው የጊዜ አጠቃቀም ውጤት ነው።

እያንዳንዱን ሰከንድ እንደ ወርቅ ሜዳሊያ ድል በመቁጠር፣ ለታቀደለት ዓላማ ማዋል የሁላችንም የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።

ጊዜን ማክበር ራስን ማክበር ነው፤ ራሱን ያከበረ ደግሞ ለስኬት የታጨ መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል በማለትም አስገንዝቧል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review