ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በደቡብ ሊባኖስ የሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ እንዲሰፋ አዘዙ

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በደቡብ ሊባኖስ የሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ እንዲሰፋ አዘዙ

AMN- መጋቢት 20/2018 ዓ.ም

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ በሰሜን እስራኤል ላይ የሚቃጣውን የሄዝቦላህ የሮኬት ጥቃት በዘላቂነት ለመግታት ወታደራዊ እርምጃው በደቡብ ሊባኖስ ይበልጥ እንዲሰፋ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ትዕዛዙ የጸጥታ ቀጣናውን በማስፋት ሄዝቦላህ በድንበር አካባቢ የሚተኩሳቸውን ፀረ-ታንክ ሚሳኤሎችና ሊሰነዝር የሚችለውን የወረራ ስጋት ለመቀልበስ መተላለፉን ገልጸዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የሄዝቦላህ ታጣቂዎችን እንዲሁም እስራኤልን ለማውደም ታቅደው የነበሩ 150 ሺህ ሚሳኤሎችንና ሮኬቶችን ማክሸፍ ችለናልም ብለዋል።

ምንም እንኳን የሄዝቦላህ አቅም ቢዳከምም፣ አሁንም ሮኬቶችን የመተኮስ ቀሪ አቅም ስላለው በሰሜን ድንበር ያለውን ሁኔታ በዘላቂነት ለመቀየር ቆርጠናል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢስራኤል ካትዝ፣ ኃይሎቻቸው እስከ ሊታኒ ወንዝ ከድንበር 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለውን ቀጣና እንደሚቆጣጠሩ ተናግረዋል።

ከፈረንጆቹ መጋቢት 2 ጀምሮ በነበረው ጦርነት ከ400 በላይ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ተገድለዋል።

በሊባኖስ በኩል በደረሰ ጥቃት ደግሞ፣ ሴቶችና ህፃናትን ጨምሮ ከ1 ሺህ 100 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በእስራኤል በኩል እስከ አሁን 4 ወታደሮች መገደላቸው እንደተገለጸ ሮይተርስ ዘግቧል።

ይህ ዘመቻ ኢራን በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖ ለማዳከም እየተካሄደ ካለው ዘርፈ ብዙ ዘመቻ አንዱ አካል መሆኑን ኔታንያሁ አክለው ገልጸዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review