“ብስክሌት በአዲስ” ወርሃዊ ፌስቲቫል ተካሄደ

You are currently viewing “ብስክሌት በአዲስ” ወርሃዊ ፌስቲቫል ተካሄደ

AMN- መጋቢት 20/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ እንዲሁም ነፍ ኢቨንትስና ኮሚዩኒኬሽን በጋራ ያዘጋጁት የ”ብስክሌት በአዲስ” ወርሃዊ የብስክሌት ፌስትቫል ተካሂዷል።

በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በየወሩ የሚካሄደው “ብስክሌት በአዲስ” ለ8ኛው ጊዜ መካሄዱን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ገልፀዋል።

ዛሬ በተካሄደው መርሐ ግብር በርካታ የብስክሌት ስፖርት አፍቃሪዎች፣ የቤተሰብ አባላት እና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ተሳታፊ መሆናቸውን አንስተዋል።

በመዲናዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለዘርፉ ምቹ መደላድል እንደፈጠረ የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፣ ዝግጅቱ ጤናማና አምራች ዜጋን በመፍጠር ማህበራዊ ትስስርንም ለማጠናከር የጎላ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዝግጅቱ በዋናነት የስፖርት ቱሪዝምን ለማሳደግና ብስክሌትን እንደ አማራጭ የትራንስፖርት ዘዴ መጠቀምን ለማስተዋወቅ ያለመ እንደሆነም ገልፀዋል።

አሁን ካለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታም አንፃር የመዲናዋ ነዋሪዎች ነዳጅን በቁጠባ ለመጠቀም ጭስ አልባ ትራንስፖርት ባህል በማሳደግ ሳይክል፣ ስኩተሮችና ሞተር አልባ የትራንስፖርት አማራጭ በማድረግ ወቅቱን በብልሃት በማለፍ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review