AMN- መጋቢት 20/2018 ዓ.ም
በከተማዋ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል ታስበው የተጀመሩት የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች፣ ነዋሪዎች ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የሚታየው ሰፊ የዋጋ ልዩነትና የአቅርቦት ትስስር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያሳደገው መጥቷል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ “አዲሱ ገበያ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ለግብይት የወጡ ነዋሪዎች ለኤ ኤም ኤን እንደገለፁት፣ የእሁድ ገበያው ከወትሮው የሰፈር ሱቆችና ሌሎች ገበያዎች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ይታይበታል ይላሉ።
ሸማች የሺሀረግ አየለ በሌላው ገበያ በኪሎ 50 ብር የሚሸጠው ቲማቲም እዚህ 30 ብር ነው፣ ሽንኩርትም እንዲሁ ኪሎ 35 ብር ነው፤ ከሌላው ገበያ በእጅጉ የተሻለ አማራጭ ሆኖልናል ይላሉ።
ሸማች ረሂማ ዱላ በበኩሏ በየሳምንቱ አስቤዛችንን የምንሸምተው በቅዳሜና እሁድ ገበያ ነው ትላለች።
መንደር ውስጥ ሁለት ኪሎ የሚገዛልን ገንዘብ እዚህ ሶስት ኪሎ ይገዛል ያለችው ረሂማ፣ ይህ ገበያ እንደ አቅማችን መግዛት እንድንችል ረድቶናል ብላለች።
ሸማች መሰረት ገመዳ በበኩሉ፣ የዋጋ ልዩነቱ ከ10 እስከ 20 ብር እንደሚደርስና ምርቱም ከአምራች ስለሚመጣ ጥራቱ አስተማማኝ እንደሆነ ተናግራለች።
ምርት አቅራቢዎች በበኩላቸው ከአምራች አርሶ አደሮች ጋር ቀጥተኛ ትስስር በመፈጠሩ ምርቶችን በቅናሽ ለማቅረብ እንደቻሉ ይናገራሉ።
ለመጪው የትንሳኤ በዓልም ምንም ዓይነት የምርት እጥረት እንደማይኖር አረጋግጠዋል።
ሸማቹ በተቀመጠው ተመን መገበያየቱን ለማረጋገጥ የክፍለ ከተማው የንግድ ባለሙያዎች ጥብቅ ክትትል እያደረጉ መሆኑን የጉለሌ ክፍለ ከተማ የንግድ ቁጥጥር እና ክትትል ባለሞያ አቶ ታዬ ታመነ ተናግረዋል።
በእያንዳንዱ የገበያ መዳረሻዎች ላይ የቁጥጥር እና የግብይት ባለሙያዎች መሰማራታቸውን በማንሳትም፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከአርሶ አደሮች ጋር በፈጠረው ትስስር ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡ እየተደረገ እንደሚገኝና ጥራቱና ዋጋውም በተቀመጠው ስርዓት መሄዱን እናረጋግጣለን ብለዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ