ፊቼ ጫምባላላ በአዲስ አበባ ከተማ ተከበረ

You are currently viewing ፊቼ ጫምባላላ በአዲስ አበባ ከተማ ተከበረ

AMN – መጋቢት 20/2018 ዓ.ም

‎የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ ጫምባላላ በአዲስ አበባ ከተማ ተከበረ፡፡

የቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ እንዳገና አበበ (ዶ/ር) ፣ ፊቼ ጫምባላላ በዓል የሲዳማ አባቶች የዘመን መለወጫን የሚያውቁበት፣ ተስፋንና መጻኢ እድልን የሚተነብዩበት፣ የአንድነትና የወንድማማችነት እሴት የታየበት ጥልቅ ፍልስፍና መሆኑንም ተናግረዋል።

የሲዳማ ብሔር የራሱ እውቀት፣ ባህልና ጥበብ ያለው ሕዝብ መሆኑንና የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር እንዳለው በመጥቀስ፤ አባቶቻችን ያወረሱን የቱሪዝም ሀብት በማጠናከር ይህ ልዩ እውቀትና ጥበብ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር በርትተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ፣ የብልጽግና መንግሥት በሀገሪቱ ውስጥ የብሔር ብሔረሰቦች ማንነት በእኩልነት እንዲጎለብት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገሪቱ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ባህልና እሴት የራሷ አድርጋ የምትቀበል፣ የምታከብርና የምትንከባከብ እንድትሆን እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፊቼ ጫምባላላ የሲዳማን ሕዝብ ቋንቋ፣ ባህልና የአኗኗር ዘይቤ ለዘመናት ጠብቆ ያቆየና የሀገራችንን ስም በዓለም አቀፍ መድረክ ያስጠራ የዓለም ሀብት መሆኑንም አስታውሰዋል።

ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ፤ የፊቼ ጫምባላላ በዓል ጥላቻን የሚያስወግድና ፍቅር የሚሰበክበት በዓል መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህን አስደናቂ እሴት ጠብቀውና ተንክባክበው ለትውልድ በማሻገር ለዛሬ ያደረሱት የሲዳማ አባቶች ክብር ይገባቸዋል ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ የአሁኑ ትውልድ ይህንን የሀገርና የዓለም ሀብት የሆነ ቅርስ ተንክባክቦ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ እንዳለበት አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች፣ የባህልና የበርካታ እሴቶች ባለቤትና ውብ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ በእነዚህ እሴቶች ልንኮራና ለሀገር ግንባታ ምሰሶ እንዲሆኑ በሥርዓቱ ልንጠቀምባቸው ይገባል ብለዋል።

በመሐመድ ቶፊቅ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review