አዲስ አበባን የገለጠው የመጋቢት ለውጥ

You are currently viewing አዲስ አበባን የገለጠው የመጋቢት ለውጥ

AMN – መጋቢት 22 /2018 ዓ.ም

መጋቢት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኡደት ውስጥ አዲስ ምዕራፍን የከፈተ የለውጥ ምዕራፍ ጅማሮ ማብሰሪያ ሆኖ ተከትቧል፡፡ በመጋቢት 24 የተበሰረው ለውጥ በፈተናዎች ውስጥ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግሩ ስኬቶችን በማስመዝገብ ዘልቋል፡፡

በዚህ የለውጥና የኢትዮጵያን ስብራቶንች የማከም ጉዞ የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ቀዳሚ ተጠቃሚና የለውጡ ተጨባጭ ፍሬ ማሳያ ነች፡፡ መዲናዋ በታሪኳ አይታው በማታውቅ ፍጥነት የመዋቅርና የገጽታ ለውጦችን እያስተናገደች ትገኛለች።

አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል ብትሆንም፣ ይህን ማዕከልነቷን የሚመጥን መሠረተ ልማት የተሟላላት አልነበረም፡፡ ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎብኚዎች የሚሆኑ በቂ መዝናኛዎችና አረንጓዴ ስፍራዎች አልነበሯትም። ከለውጡ ወዲህ ግን ይህ ታሪክ እጅጉን ተቀይሯል።

አንድነት፣ ሸገር፣ እንጦጦ እና ወዳጅነትን የመሳሰሉ ግዙፍ ፓርኮችን አዲስ አበባ ያገኘቸው በእነዚህ የለውጥ ዓመታት ነው። ፓርኮቹ ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ከማድረግ ባለፈ ፣ ለነዋሪዎቿ የተመቸች እንድትሆን አስችሏታል፡፡

እንደ አብርሆት ቤተ-መጻህፍት እና የሳይንስ ሙዚየም ያሉ ግዙፍ ተቋማት መገንባታቸው አዲስ አበባን የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ ለተያዘው ግብ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡

የኮሪደር ልማት ደግሞ የአዲስ አበባን ገጽታ ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል። ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መስመሮች እና ዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራቶች ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹና ማራኪ አድርገዋታል።

ከማራኪነትም ባሻገር ለስራ ፈጠራ ፣ ለቢዝነስ እንቅስቃሴ የምትመች ስልጡን ከተማ እንድትሆን መሠረተ ልማቶችን ገንብታለች፡፡

የመሠረተ ልማት ዝርጋታው የትራፊክ ፍሰትን ከማሳለጡም በላይ የምሽት ንግድና እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ምቹ ሆኔታን የፈጠረ ነው፡፡

በታደሰ ሽፈራዉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review