AMN – መጋቢት 22/2018 ዓ.ም
ከለዉጡ ወዲህ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሃገሪቱ እየተተገበሩ በሚገኙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች በርካታ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት እና የተለያዩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ አቅመ ደካማ ዜጎችን እና የሃገር ባለዉለታዎችን ከመደገፍ፤ የመኖሪያ ቤት እንዲታደስላቸዉና እንዲገነባላቸዉ በማድረግ ረገድ በርካታ ሥራዎች ተከናዉነዋል፡፡
ከለዉጡ ወዲህ የመዲናዋን ባለሃብቶች፤ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ ክረምት ከበጋ እና በመደበኛ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሰሩ ሥራዎች ከ45 ሺህ 566 በላይ ቤቶች መገንባታቸዉን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል፡፡

እነዚህ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ከአሁን ቀደም በሃገሪቱ ያልተለመዱ ከመሆናቸዉ የተነሳ ነዋሪዎቹ የመኖሪያ ቤት እናገኛለን፤ እምባችን ይታበሳል፤ ከወደቅንበትም እንነሳለን የሚል ግምትም እንዳልነበራቸዉ ይናገራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸዉን እና ደጋፊ የሌላቸዉን ወገኖች ጨምሮ በርካታ የሃገር ባለዉለታዎችን የመኖር ተስፋ ያለመለሙ ከመሆናቸዉም ባሻገር በህብረተሰቡ ዘንድ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህል እንዲጎለብት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
በጎነት በተግባር የተገለጠበት የመጋቢት ወር የዘመሙ ጎጆዎችን በማቃናት ቤት ብቻ ሳይሆን በምገባ አገልግሎት፤ በበአላት ወቅት ድጋፍ እና በመሰል ድጋፎች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ