”አዲስ አበባ ከተማ ለእኔ እንደ ገነት ናት” – ካሜሮናዊው ቱሪስት አተም ሃሪስ

You are currently viewing ”አዲስ አበባ ከተማ ለእኔ እንደ ገነት ናት” – ካሜሮናዊው ቱሪስት አተም ሃሪስ

AMN – መጋቢት 22/2018 ዓ.ም

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ፣ በኮሪደር ልማት በተዋበው ዘመናዊ ገጽታዋ እና በጥልቅ ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴቶቿ የብዙ ሀገራት ጎብኚዎችን ቀልብ መማረኳን ቀጥላለች።

በቅርቡ ከተማዋን ከጎበኙ አንግዶች መካከል ካሜሮናዊው የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ አታም ሃሪስ አንዱ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ለየት የሚያደርጋት ውበት እንዳላትና “እንደ ገነት” የምትቆጠር ከተማ መሆኗን ገልጿል።

አተም ሃሪስ በቆይታዉ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ስፍራዎችን ጎብኝቷል።

ከነዚህም መካከል የመንፈሳዊነትና የታሪክ ጥምረት ጉብኝቱ አካል በሆነው በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተገኝቶ ያየው ሃይማኖታዊ ስርዓት አንዱ ነበር።

ቤተክርስቲያኑ እና የህንፃው ውበት ልዩ እና መንፈሳዊ ስሜት እንደፈጠረበት ገልጾ፣ ጥልቅ የሆነ ሰላምና መንፈሳዊነት የሚገኝበት ስፍራ እንደሆነም አክሏል።

ካሜሮናዊው የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ አታም ሃሪስ ከቤተክርስቲያን ጉብኝት በኋላ ወደ አድዋ ድል መታሰቢያ አቅንቷል።

የኢትዮጵያ ጀግኖች ለነጻነታቸዉና ለሃገራቸዉ ሉአላዊነት የከፈሉትን መስዋዕትነት ከታሪክ መዘክሮች መረዳቱን ይገልጻል።

የኢትዮጵያውያን ጀግንነት የፈጠረበትን ጥልቅ ስሜት የሚናገረዉ አታም ሃሪስ ለጀግኖች አርበኞች ያለውን ታላቅ አክብሮትም ገልጿል።

አተም ሃሪስ የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ሙዚቃና ጣፋጭ ምግቦች ከሚገኙባቸው የመዲናዋ ባህላዊ ምግብ ቤቶች መካከል አንዱ በሆነው “ቶቶት” ባህላዊ የምግብ አዳራሽ ተገኝቶ በተመለከተዉ የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ዜማና ጭፈራ መደሠቱን አስረድቷል።

ካሜሮናዊው ባደረገው ጉብኝት አዲስ አበባ ከዘመናዊ ህንፃዎቿ ባሻገር፣ ጥልቅ ታሪክና ሕያው ባህል ያላት ከተማ መሆኗን ያረጋገጠበት እንደሆነ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review