AMN መጋቢት 21/2018 ዓ.ም
ኢራን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን ካልከፈተች የሃይል ማመንጫዎቿ እና የነዳጅ ጉድጓዶቿ እንደሚደመሰሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ።
ትራምፕ ይህን ያሉት ቴህራን የዩናይትድ ስቴትስን የሰላም ጥያቄ “ከእውነታ የራቀ” ካለችና ወደ እስራኤል በርካታ ሚሳኤሎችን ካስወነጨፈች በኋላ ነው።
የእስራኤል ጦር ሰኞ ዕለት ከየመን የተተኮሱ ሁለት ድሮኖችን ማክሸፉን አስታውቋል። ይህም የሆነው ከኢራን ጋር የሚወግኑት ሁቲዎች ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን በመተኮስ ጦርነቱን ከተቀላቀሉ ከሁለት ቀናት በኋላ ሲሆን፣ የሊባኖሱ ሄዝቦላህም ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ተኩሷል።
የእስራኤል ጦር በቴህራን በሚገኙ ወታደራዊ መሰረተ ልማቶች እና በቤሩት በሚገኘው የሄዝቦላህ ይዞታ ላይ የሚሳኤል ጥቃት የሰነዘረ ሲሆን፣ በሊባኖስ ዋና ከተማ ላይ ጥቁር ጭስ ሲያንዣብብ ታይቷል።
በአሜሪካ -እስራኤል ጥቃት የተጀመረውና አንድ ወር የሞላው ጦርነት ወደ ቀጠናው እየተስፋፋ ባለበት ወቅት ኢራን አሁንም አቋሟን አልቀየረችም።

ይህ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገ፣ የኃይል አቅርቦትን ያወከ እና የአለምን ኢኮኖሚ የጎዳ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ሟቾች በኢራን እና በሊባኖስ የሚገኙ ሲቪሎች መሆናቸዉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኢራን የአለምን አንድ አምስተኛ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት የሚያልፍበትን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን ዘግታለች።
ኢራን በፓኪስታን፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኩል የተላከላት የዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ጥያቄ እንደደረሳት አስታውቃለች።
ሆኖም የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጥያቄዎቹ “ከእውነታ የራቁ፣ ምክንያታዊ ያልሆኑ እና ከልክ ያለፈ ፍላጎት ያረፈባቸው” ናቸው ብለዋል።
“አቋማችን ግልጽ ነው። ወታደራዊ ጥቃት እየተፈጸመብን በመሆኑ፣ ጥረታችን እና ጥንካሬያችን ሁሉ እራሳችንን በመከላከል ላይ ያተኮረ ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ከመግለጫ በኋላ ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ያለውን ጦርነት ለማቆም “የተሻለ አእምሮ ካለው አገዛዝ” ጋር ንግግር እያደረገች መሆኑን ገልጸው፣ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ ግን አዲስ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ትራምፕ “ትልቅ መሻሻል ታይቷል፤ ነገር ግን በማንኛውም ምክንያት በአጭር ጊዜ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ እና የሆርሙዝ ወሽመጥ ወዲያውኑ ለንግድ ክፍት ካልሆነ፣ ሁሉንም የኤሌክትሪክ ማመንጫዎቻቸውን፣ የነዳጅ ጉድጓዶቻቸውን እና የካርግ ደሴትን በማጥፋት በኢራን ያለንን ቆይታ እናበቃለን።”
ትራምፕ በተጨማሪም ለኢራን ንጹህ ውሃ የሚያቀርቡ የጨው ውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎችን እንደሚያጠቁ ነዉ የዛቱት፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ