AMN- መጋበት 22/2018 ዓ.ም
የከነማ ፍርማሲዎች ድርጅት የካንሰር መድሀኒቶችን ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የሚያግዝ የመጀመርያ የሆነውን የካንሰር ህክምና ልዩ መድሃኒት ማዕከል አስጀመረ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ያነሱት የአዲስ አበባ የመንግስት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር ባለስልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቅሬ ግዛው፣ ህክምናው በተሟላ መልኩ እንዲሰጥ ጤና ተቋማትን ከማስፋፋት ባሻገር የመድሃኒት አቅርቦት ሌላው የትኩረት ማእከል መሆኑን ተናግረዋል።
የጀመርያ የሆነውን የካንሰር ህክምና ልዩ መድሃኒት ማእከልን ማስጀመር በመድሃኒት አቅርቦት መስክ የሚነሱ ጥያቄዎችን የመመለስ አንድ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግስት በቀጣይም እጥረት የሚታይባቸውን መስኮች በመለየት ወደ ማህበረሰቡ ይበልጥ ለመቅረብ ጥረቶችን እንደሚቀጥልም አቶ ፍቅሬ ግዛው አስታውቀዋል።
የከነማ ፋርማሲዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይፈ ደምሴ በበኩላቸው፣ ካንሰር እንደዓለም ፈተና የሆነ ህመም መሆኑን በማንሳት ህክምናው በሀገራችን ውስን ቦታዎች ብቻ የሚሰጥ እና የመድሃኒት እጥረትም የሚታይበት ነው ብለዋል።
በማህበረሰቡ በተደጋጋሚ የሚነሱ የሙድሃኒት ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲረዳ የተከፈተው ማዕከሉ፣ በቀጣይም በተለያዩ አካባቢወች የማህበረሰቡን ፍላጎት የሚያረኩ ቅርንጫፎችን ለመክፈት እቅድ እንዳለውም አቶ ሰይፈ ደምሴ ገልጸዋል።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒፓል አቅራቢያ የተከፈተው የመጀመርያው ማዕከል በርካታ ታካሚዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳም ተናግረዋል።
ማህበረሰቡ ህክምናውን በሚገባ በመከታተል መድሃኒቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እና ጤናማ ማህበረሰብን በመፍጠር ካንሰርን ለመዋጋት የማዕከሉ መከፈት የጎላ ድርሻ እንዳለው ተመላክቷል።
በቤተልሔም አየነው