AMN- መጋቢት 23/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ካከናወነቻቸው ሪፎርሞች አንዱ የግብርናው ዘርፍ ተጠቃሽ ነው። በለውጡ ዓመታት በግብርናው ዘርፍ በተዘጋጀው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ በትኩረት ከሚሰራባቸው አስር የሰብል አይነቶች አንዱ ስንዴ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ አንድ ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጭ በማድረግ የስንዴ ምርትን ወደ ሀገር ውስጥ ስታስገባ መቆየቷን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት የተተገበረው ስንዴን በበጋ እና በክረምት በስፋት በማልማት የሀገር ውስጥ ፍጆታን በማሟላት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ተችሏል። እንዲሁም ስንዴን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማዳን በስንዴ ልማት ላይ በትኩረት በመሰራቱ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በመስኖ የለማ ስንዴ በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 20 ሺህ ሄክታር መሬት፣ በ2017 ምርት ዘመን ወደ 3.5 ሚሊየን ሄክታር ዕድገት አሳይቷል፡፡ ምርቱንም ከ600 ሺህ ኩንታል ወደ 128 ሚሊየን ኩንታል ማሳደግ ተችሏል፡፡
በመኸር ወቅት የለማ ስንዴ በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 1.8 ሚሊየን ሄክታር በ2017 ምርት ዘመን ወደ 4.3 ሚሊየን ሄክታር ማሳደግ የተቻለ ሲሆን፣ ምርቱንም ከነበረበት 53 ሚሊየን ኩንታል ወደ 152 ሚሊየን ኩንታል ማድረስ ተችሏል። በአጠቃላይ በ2017 በጀት ዓመት በስንዴ የለማ መሬት 7.8 ሚሊየን ሄክታር በመሸፈን 280 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ተመርቷል፡፡

በየዓመቱ በውጭ ምንዛሬ ይገባ የነበረው ስንዴ በ2017 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት የተቻለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት በአማካይ ታወጣ የነበረውን አንድ ቢሊየን ዶላር ማስቀረት ተችሏል::
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ብሄራዊ የስንዴ ልማት ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው ስንዴ በራስ አቅም በማምረት ራስን ከመቻል ባለፈ ከአፍሪካ ቀዳሚ የስንዴ አምራች ሀገር አድርጓታል ማለታቸው ይታወቃል::
እንደ ሀገር በስንዴ ራስን ለመቻል በተሠራዉ ሥራ እና ስኬታማ ኢኒሼቲቭ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጣሊያን ሮም በተካሄደው የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት አግሪኮላ ሜዳሊያ ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም መሸለማቸው ይታወሳል።
በያለው ጌታነህ