በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተው ጦርነት ያስከተለውን ዓለም አቀፋዊ የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለመቋቋም ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አሰራሮችን በመተግበር ላይ ነው

You are currently viewing በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተው ጦርነት ያስከተለውን ዓለም አቀፋዊ የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለመቋቋም ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አሰራሮችን በመተግበር ላይ ነው

AMN – መጋቢት 23/2018 ዓ.ም

በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን ዓለም አቀፋዊ የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለመቋቋም፤ የከተማ አስተዳደሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዋቀረውን አደረጃጀት ተከትሎ በምክትል ከንቲባው የሚመራ ግብረ ኃይል በማደራጀት ወደ ስራ ገብቷል።

ይህ ግብረ ኃይል በዛሬው እለት ሁለት መድረኮችን በማዘጋጀት በጉዳዩ ላይ ሰፊ ምክክር ያደረገ ሲሆን፤ የከተማዋ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ የቀጣይ ስራ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።

በዚሁ መሠረት በትራንስፖርት፣ በፋይናንስና በፀጥታ ተቋማት በኩል የግንዛቤ ፈጠራ ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተወሰኗል።

በተጨማሪም የትራፊክ ማኔጅመንትና የትራፊክ ፖሊስ አባላት በማደያዎች አካባቢ የሚስተዋለውን ረጅም ሰልፍ በሚያቃልሉበትና በሚያስተካክሉበት ሁኔታ ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በየማደያው የተሟላ የመረጃ ተደራሽነት እንዲኖር የከተማው ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት አሰራር እንዲዘረጋ፣ እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን ወቅታዊ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በመድረኩ ላይ የካፒታል ፕሮጀክቶችን የሚመሩ ተቋማት የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ስራዎች እንዲለዩና ከተቋራጮች ጋር እንዲወያዩ ከመደረጉም ባለፈ፤ የግንዛቤ ፈጠራን፣ የተሽከርካሪ ስምሪትን እንዲሁም የነዳጅ አጠቃቀምና ቁጥጥርን መሰረት ያደረጉ ውይይቶች መካሄዳቸውን የአዲስ አበባ ኮሚኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review