ያለደረሰኝ ግብይት የፈፀሙ 55 ግብር ከፋዮች እስከ ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ

You are currently viewing ያለደረሰኝ ግብይት የፈፀሙ 55 ግብር ከፋዮች እስከ ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ

AMN – መጋቢት 23/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓትን ለማስፈንና ለከተማዋ ልማት የሚውል ገቢን በብቃት ለመሰብሰብ፣ ያለደረሰኝ ግብይት በሚፈፅሙ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አስታወቀ።

ቢሮው ባለፉት ስምንት ወራት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ ባካሄደው ተከታታይ የክትትል ሥራ፣ ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የተገኙ 294 ተጠርጣሪዎችን እጅ ከፍንጅ መያዙን ገልጿል።

ክትትሉ በተለይም በጎማና መኪና መለዋወጫ፣ በኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ በኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ በሥጋ ቤቶች፣ በአልባሳት እንዲሁም በወለል ምንጣፍ ንግድ ላይ በተሰማሩ ግብር ከፋዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተጠቁሟል።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከል የ55ቱ ጉዳይ በሕግ ታይቶ ውሳኔ ያገኘ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም የመንግስትን ጥቅም በማሳጣትና የታክስ አስተዳደር አዋጅን በመጣስ ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ባገኛቸው ግለሰቦች ላይ ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት የሚደርስ ፅኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት አስተላልፎባቸዋል።

ቀሪዎቹ 239 ተጠርጣሪዎች በአሁኑ ወቅት ክስ ተመስርቶባቸው በፍርድ ቤት የክርክር ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በኦዲት ምርመራ ዳግም ተጠያቂ እንዲሆኑ የተደረጉ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ተመላክቷል።

ቢሮው በቀጣይም ያለደረሰኝ የሚከናወን ግብይትንና የግብር ስወራን ለመከላከል፣ የንግድ ሥርዓቱን ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት የጀመረውን የክትትል ተግባር በሌሎችም የሥራ ዘርፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የንግዱ ማህበረሰብ ማንኛውንም ግብይት በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅም ያሳሰበው ቢሮው፤ ህብረተሰቡም መሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት በ7075 ነፃ የጥሪ መስመር በመጠቀም ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቢሮው ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በላከው መረጃ ጥሪ አቅርቧል ፡፡።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review