AMN- መጋቢት 23/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የኢንተር ፕራይዞች ምርታማነት ለሀገር ብልፅግና በሚል መሪ ሀሳብ ሳምንታዊ የኢንተርፕራይዝ ባዛር መክፈቻ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ፣ መንግስት ለዜጎች የስራ ዕድልን ለማስፋት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ጊዜያት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
በዚህም አምራች ኢንተርፕራይዞች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ተኪ ምርቶችን በማምረት ለገበያ በማቅረብ ረገድ ሚናቸው የጎላ ስለመሆናቸው አንስተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለኢንተርፕራዝ አምራቾች አሰፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በሀገር ውስጥ ምርቶች የመኩራትና የመጠቀም ባህላችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ ይገባል ብለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ፣ የኢንተርፐራይዝ ሳምንት ባዛሩ እርስ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበትና ለአምራቾቹ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት ነው ብለዋል።
የኢንተርፕራይዞችን ምርታማነት በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።
ባዛሩ በከተማ ደረጃ የተዘጋጀ ሲሆን፣ 300 የሚደርሱ አምራች ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የምግብ ምርቶችና የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ባዛሩ ከመጋቢት 23 እስከ 27 እንደሚቆይ ተገልጿል።
በመሀመድኑር ዓሊ