AMN – መጋቢት 23/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት ያስመዘገበቻቸው ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ በቀጣናዊና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተሰሚነት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረዋል።
ይህ የዲፕሎማሲ ጉዞ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በማፅናትና አዳዲስ ስልታዊ አጋርነቶችን በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በኢትዮጵያ የሰላም ዲፕሎማሲ ውስጥ እንደ ቀዳሚ ስኬት የሚጠቀሰው ከቀጣናው ሀገራት ጋር የነበሩ ቅራኔዎችን በመፍታት የዲኘሎማሲ ግንኙነቱን ውጤታማ ማድረግ መቻሉ ተጠቃሽ ነው፡፡
ይህም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኖቤል ሰላም ሽልማትን ከማስገኘቱም በላይ ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት መካከል ለሚፈጠሩ ግጭቶች ያላትን የአደራዳሪነትና የሰላም አስከባሪነት ሚና እንድታጠናክር አስችሏታል። በሌላ በኩል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና የውኃ ሙሌት ሂደት የሀገሪቱን የሉዓላዊነት ዲፕሎማሲ የፈተነ ታላቅ ክስተት ነበር።
ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በነበራት የረጅም ጊዜ ድርድር የውጭ ጫናዎችን በጽናት በመቋቋም ግድቡን በራሷ አቅም የመገንባትና የመሙላት መብቷን በተግባር አረጋግጣለች።
ይህም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን መርህ በማፅናት በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር የሚደረጉ ድርድሮች ውጤታማ እንዲሆኑ አዲስ መንገድ ከፍቷል።
በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት በታሪክ የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይም የ(በቃ) ንቅናቄን የመሰሉ ዓለም አቀፍ ድምጾች የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመመከት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በኢኮኖሚና በባለብዙ ወገን ትብብር ረገድም አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር ሆና መመረጧ በኢኮኖሚ ካደጉና ታዳጊ ከሆኑ ሀገራት ጋር ያላትን ትስስር የሚያጠናክር ስልታዊ ስኬት ነው። ይህም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የሀገሪቱን የንግድ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት ካጋጠሟት ዲፕሎማሲያዊ ማዕቀቦችና ጫናዎች ወጥታ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መድረክ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገሯ ተረጋግጧል።
በበረከት ጌታቸው