ለአራት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የሰርከስ ፌስቲቫልና ውድድር በደማቅ ሁኔታ ተጠናቀቀ

You are currently viewing ለአራት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የሰርከስ ፌስቲቫልና ውድድር በደማቅ ሁኔታ ተጠናቀቀ

AMN መጋቢት 24/2018

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ኪነ ጥበብ ቢሮ የኪነ ጥበብ ዘርፉን ለማስተዋወቅ : በዘርፉ ላሉ ባለሙያዎች እድሎችን ለመፍጠር እና አዳዲስ ባለተሰጥኦዎችን ለማፍራት የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።

ቢሮዉ የከተማዋን የባህል ገጽታ ለማጠናከር “የሰርከስ ጥበብ ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የሰርከስ ፌስቲቫልና ውድድር ለተከታታይ አራት ቀናት በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ሲያካሄድ ቆይቷል። ይህ ፌስቲቫልና ዉድድር በኢትዮጵያ የሰርከስ ጥበብ እድገት ውስጥ ጉልህ ምዕራፍ በማስመዝገብ በዛሬዉ ዕለት ተጠናቅቋል።

መድረኩ የሰርከስ ጥበባት ፈጠራን እና ሰፊውን የኪነጥበብ ዘርፍ በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ኪነጥበብ ቢሮ ሀላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ተናግረዋል። የተለያዩ የሰርከስ ማህበራት በፌስቲቫሉ የተሳተፉ ሲሆን፣ ይህም በከተማ ደረጃ የተካሄደ የመጀመሪያው አይነት ዝግጅት እንዲሆን አድርጎታል።

ውድድሩ አካላዊ ጥንካሬን እና የአፈጻጸም ክህሎቶችን ከማሳየት ባለፈ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ሊወክሉ የሚችሉ ከፍተኛ ችሎታ ያላቸውን የሰርከስ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደ ማሳያ ሆኖ ያገለግላል ሲሉ ኃላፊዋ ተናግረዋል ።

የውድድሩ አሸናፊዎች የገንዘብ እንዲሁም የወርቅ እና የነሐስ ሜዳሊያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል። በዝግጅቱ ላይ የታደሙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ዝግጅቱን ባማረ መልኩ ላዘጋጁ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

እውቅናው የተወዳዳሪዎችን ስኬት ከማስተዋወቁም ባሻገር ከተማዋ የሰርከስ ጥበብ ዘርፍን ለመደገፍ እና ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት አጉልቶ አሳይቷል። ፌስቲቫሉ ከ280 በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበት የመዲናዋ ልዩ የሰርከስ የፍፃሜ ውድድር ሆኖ ተጠናቅቋል ።

በንግስት ዘውዱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review