AMN – መጋቢት 24/2018 ዓ.ም
ባለፉት ስምንት ዓመታት የተመዘገቡት የልማት ሥራዎች፣ የተገቡ ቃሎች ሁሉ በተግባር ተፈጽመው ማየታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በለዉጡ መንግሥት የተከናወኑ ተግባራትንና በመዲናዋ የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን በመደገፍ ደማቅ ትዕይንተ ህዝብ አካሂደዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት ነዋሪዎች በተለይም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያና በመዲናዋ የታዩት የልማት ስራዎች የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ እመቤት አበራ “ቃልን በተግባር ያደረገ የማያሳፍረን መሪ አለን” ብለዋል። የለዉጥ አመራሮቹ የገቡትን ቃል በተግባር ፈጽመው በማሳየታቸው ትልቅ አድናቆት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
የለሚኩራ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ብሩክ መኮንን በበኩላቸው፣ ቀድሞ የነበረችው አዲስ አበባ ለመዝናናት አመቺ እንዳልነበረችና የጤና ችግር የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ይበዙባት እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ግን ልጆች በነፃነት የሚጫወቱባቸው አረንጓዴ ስፍራዎች መበራከታቸውንና ወላጆችም ልጆቻቸውን እያጫወቱ መጽሐፍ የሚያነቡበት ምቹ ዘመን ላይ መድረሳቸዉን ገልጸዋል።

ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመጡት ወ/ሮ ሮማን ወልዴ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከናወኑ ስራዎች በ80 ዓመታት ውስጥ ይሆናሉ ተብለው የማይታሰቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይም በቅርቡ የተመረቀው የ”መሶብ” አገልግሎት የታቀደው በፍጥነት ወደ ተግባር መቀየሩን እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል።
ሌላኛዋ ነዋሪ ወ/ሮ ፀሐይ ብሩ የመንግስት ስራ አስፈጻሚዎች ተባብረው ጎርፍና ዝናብ ይፈታተናት የነበረውን መኖሪያ ቤታቸውን ቀይረው በተሻለ ቤት እንዲኖሩ በማድረጋቸው ዛሬ በተሻለ ህይወት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ማቲዮስ ብርሃኑ ቀድሞ የነበሩ የአገልግሎት መጉላላቶች በ”መሶብ” አንድ ማዕከል አገልግሎት መፈታታቸውን ገልጸዋል።
ሰልፈኞቹ በመዲናዋ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡ ።
በታደሰ ሽፈራው