AMN – መጋቢት 24/2018 ዓ.ም
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት የሰላም ጋሻ፣ የብሔራዊ ክብርና ጥቅማችን ዘብ ናቸው ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ “የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ቅንጅት ለሀገራዊ ሰላም እና ደኅንነት” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ብሔራዊ የደኅንነት ኮንፍረንስ ላይ ተሳትፈናል ብለዋል።
በቀጣናችን የሚስተዋሉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች፣ የአሸባሪ ቡድኖች ሴራ፣ የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትና ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች ሀገራችንን ቢፈትኑም፤ በፀጥታና ደኅንነት ተቋሞቻችን ጥንካሬና በልጆቿ መስዋዕትነት ለአፍሪካ ፋና ወጊ የሚሆን ተግባር በመፈፀም ዛሬም እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያ ጸንታ ቆማለች ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የጸጥታና ደኅንነት ተቋሞቻችን ችግርን ወደ ዕድል እንዲቀየሩ ያስቻሉ ናቸው፡፡ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይልና በአደረጃጀት የዘመኑት የጸጥታ ኃይሎቻችን ሌት ተቀን ትጋት እና በህዝባችን አጋርነት አገራዊ ሁለንተናዊ ውጤት ማስመዝገብ ያስቻለን ነው ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር የምናደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊና ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴዎች ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል ብለዋል፡፡
ይህን ስኬት ለማስመዝገብ ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ የፌደራል የፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም የክልል የፀጥታ ተቋማት ቅንጅትና የጋራ ጥረት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።
በሌላ በኩል በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሰላምን ለማስፈን የተሄደባቸው ርቀቶችና የተገኙት ውጤቶች የሚበረታቱ ሲሆኑ፣ በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማትና የሕዝቡ የተቀናጀ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ የምናካሂደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ዴሞክራሲን የምናጸናበት ታሪካዊ ምዕራፍ እንዲሆን የጸጥታ ተቋሞቻችን ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንደሚወጡ እምነቴ የጸና ነው።
ጉዟችን ተጀመረ እንጂ አልተቋጨምና ከትናንት ዕዳዎች ተላቀን፣ የዛሬ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን ለነገው ትውልድ የምትመጥን ሀገር ለመገንባት በዓላማ ጽናት እንቀጥላለን።
ለሀገር ህልውና መስዋዕትነት ለከፈሉና ሌት ተቀን ለሚተጉ የጸጥታና ደኅንነት አመራሮችና አባላቶቻችን እንዲሁም በሀገሩ ጉዳይ ለማይደራደረው ለጀግናው ሕዝባችን ያለኝን ጥልቅ አክብሮት መግለጽ እወዳለሁ ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።