ከሸማችነት ወደ አምራችነት የተመዘገበ እመርታ

You are currently viewing ከሸማችነት ወደ አምራችነት የተመዘገበ እመርታ

AMN – መጋቢት 24/2018 ዓ.ም

መንግስት ባለፉት ስምንት ዓመታት ባከናወናቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎች የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአዝጋሚ ጉዞ ወደ ስር ነቀል ለውጥ ተሸጋግሯል።

በተለይም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግና የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ የተጀመረው “ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገራዊ ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪው ምቹ መደላደል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡

በዚህም በለውጡ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተወሰዱ የሪፎርም ማሻሻያዎች ቀደም ሲል ከ47 በመቶ የማይበልጠው የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አሁን ላይ ወደ 66.3 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡

የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ሊያስወጣ ይችል የነበረን የውጭ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል። እንዲሁም መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች ስራ አቁመው የነበሩ 917 ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ውጭ የመላክ አፈጻጸም በሁለት እጥፍ ዕድገት አሳይቷል።

በመዲናችን አዲስ አበባም ከአቅም በታች ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች አሁን ላይ የለውጡ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩርት የማምረት አቅማቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። በዚህም በሺዎች ለሚቆጠሩ የከተማዋ ወጣቶች የሥራ ዕድልን ፈጥሯል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ መንደሮችን በማስፋፋት ለአምራቾች ምቹ የስራ ቦታ ያመቻቸ ሲሆን ለኢንተርፕራይዞች የማሽነሪ ግዢ የሚውል የሊዝ ፋይናንስና የብድር አገልግሎት እንዲመቻች እና የቢሮክራሲ ማነቆዎችን የሚፈታ “የአንድ ማዕከል” አገልግሎት እንዲቋቋም አድርጓል።

በአጠቃላይ ባለፉት 8 አመታት መንግሥት ባደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ እና የፋይናንስ ድጋፍ ኢንዱስትሪው ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሆኗል፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review