ከቁጥር ባለፈ የዜጎች ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ሁለንተናዊ እመርታ

You are currently viewing ከቁጥር ባለፈ የዜጎች ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ሁለንተናዊ እመርታ

AMN – መጋቢት 24/2018 ዓ.ም

ብልፅግና በቁጥር የሚገለጽ የሀብት ክምችት ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽልና ሰብአዊ ክብርን የሚያረጋግጥ ሰፊ ማዕቀፍ ነው።

እንደ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ገለጻ፣ የአንድ ሀገር እድገት የሚለካው በገንዘብ ክምችት ብቻ ሳይሆን ዜጎች በሚኖራቸው ረጅም እድሜ፣ እውቀትና የተመቻቸ ኑሮ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት በበርካታ ዘርፎች የጀመረችው ሁለንተናዊ የስኬት ጉዞ በቁጥር ከሚገለጽ የኢኮኖሚ ዕድገት ባለፈ፣ ወደ ተጨባጭ ውጤቶች እየተሸጋገረ ይገኛል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ራሷን መቻል ብቻ ሳይሆን ምርቷን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ጀምራለች። ይህ ጅማሮ ሀገሪቱ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ላስቀመጠችው ግብ ታላቅ ስኬት ሲሆን፣ ቀደም ሲል ለስንዴ ግዢ ታወጣው የነበረውን ወጪ በእጅጉ ለመቆጠብ አስችሏል፡፡

የከተሞችን ውበትና ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የተጀመረው የኮሪደር ልማትም ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ፣ የንግድ እንቅስቃሴንና የቱሪስት ፍሰትን የሚጨምሩ ዘመናዊ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን እንዲያሟላ ተደርጓል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል መቻሏ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አፕልና ፓፓያ ያሉ የፍራፍሬ ልማቶችን በማስፋፋት ለገበሬው አዲስ የገቢ ምንጭ ፈጥሯል።

የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅና አገልግሎት መስጠት መጀመሩ በሀገር ውስጥ ለሚገኘው የኢንዱስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚ መነቃቃትና ለቀጣናዊ የኃይል ትስስር ዋነኛ ምሰሶ ሆኗል።

እንደ ገበታ ለሀገር፣ ወንጪ፣ ጎርጎራና ኮይሻ የመሳሰሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች መገንባታቸው ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ቱሪዝም ያላትን አቅም ለዓለም እንድታሳይ አስችሏታል።

ኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ ተግባራዊ ያደረገችው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ ሲሆን ለወጣቱም ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ የልማት ስራዎችና የተገኙ ስኬቶች የብልፅግና ጉዞን እውን በማድረግ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ ናቸው፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review