AMN መጋቢት 24/2018 ዓ.ም
ከመጋቢት 2010 እስከ መጋቢት 2018 ዓ.ም. ባሉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸዉ ድሎች ጥቂቶቹ
የለውጡ መንግሥት የልዩነትና የግጭት መንስኤ የሆኑትን ነጠላና ሃሰተኛ ትርክቶችና በአሰባሳቢና በወል ትርክቶች ለመተካት በሰራው ስራ የጋራ መግባባትን መፍጠር የሚያስችሉ ስኬቶች ተገኝተዋል፡፡ ጥላቻ፣ ዘረኝነት ፣ ጽንፈኝነት፣ አግላይነት፣ ጠቅላይነት እና መሰል ከፋፋይ እሳቤዎች የሃገረ መንግስት እና የብሄረ መንግስት ግንባታ አደጋዎች መሆናቸዉን ከመግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራዊ ምክክር በማካሔድ ላይ ትገኛለች፡፡ እስካሁን ድረስ በተካሄዱ አጀንዳ የማሳባሰብ የምክክር ሂደቶች ህብረተሰቡ እና የተለያዩ አካላት ሊፈቱ ይገባል ያሏቸዉን አጀንዳዎች አቅርበዋል፡፡ ሃገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ለዘመናት ያልተፈቱት ፖለቲካዊ እና መሰል ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት በቁርጠኝነት በመስራት ላይ የምትገኝ ስትሆን ሌብነትንና አድልዎን የሚያስቀር በቴክኖሎጂ የታገዘ የመንግስት አገልግሎት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በመስጠት ላይ ትገኛለች፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂዉ ዘርፍ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ፣ ዲጂታል ግብይት እና ዲጂታል የመታወቂያ አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ የአሰራር ስርአቶችን ተግባራዊ በማድረግ ደጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ ለበርካቶች ምሳሌ መሆን የሚችል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዳለች፡፡ መራጮች በምሽት ጭምር ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመሄድ እና ለረጅም ጊዜ በመሰለፍ ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚዉ ዘርፍ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግባለች፡፡ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተግባራዊ ባደረገቻቸዉ ሪፎርሞች የኢኮኖሚውን ዘርፍ እመርታን ማረጋገጥ ችላለች፡፡ ከወጪ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ጨምሮ ከተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ ገቢ ማስመዝገብ ችላለች፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመከላከል ከለዉጡ ወዲህ በጀመረችዉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አለም አቀፍ እዉቅናን ያገኘች ሲሆን ችግኝ መትከል ባህል ከመሆን አልፎ ለተቀረው ዓለም መልካም ተሞክሮ ሆኗል።
ከለዉጡ ወዲህ የጦር መሳሪያ አንስተዉ ፣ ጫካ ገብተው ሲታገሉ የነበሩ ቡድኖች በመንግሥትና በሕዝብ የቀረበላቸዉን የሰላም ጥሪ ተቀብለዉ መመለስ ችለዋል፡፡ ነፍጥ ያነሱ በርካታ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ መንገድ ተመልሰው፤ የተሃድሶ ስልጠና ወስደዉ ወደ መደበኛ ህይወታቸዉ መመለስ ችለዋል
ኢትዮጵያ ዉስጥ የሃሳብ እና የፖለቲካ ልዩነቶችን ከጦር መሳሪያ አፈሙዝ ይልቅ በንግግር እና በዉይይት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ጅማሮች ታይተዋል፡፡ ከተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በሃገር ዉስጥ እና በውጭ ሃገራት ፍሬያማ ዉይይቶች ተደርገዋል፡፡ የሰሜኑን ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በመቋጨት ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በማምጣት ለተቀረው ዓለም ምሳሌ ሆናለች።
በወንድማገኝ አሰፋ