“የተሰበሩ ማህበራዊ እሴቶችን በማከም ማህበራዊ ፍትሕ እንዲነግስ የሚያስችሉ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል”
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ልክ ከዘመናት እንቅልፍ እንደመንቃት፣ አሊያም የመቃብርን ድንጋይ ፈንቅሎ እንደመውጣት፣ በድቅድቅ ጨለማ እንደሌት ጨረቃ ፈክቶ እንደመታየት፣ ጉስቁልናውን እና እርጅናውን አሽቀንጥሮ ጥሎ በማራኪ ውበት፣ በአስደማሚ ጉልበት ታጅቦ እንደሚነሳ ንስር አሞራ የኋላ ቀርነትን ጨለማ ሰብራ እንደ ንጋት ኮከብ ደምቃ ትታያለች፡፡
በተለይም ሰውን ማዕከል ባደረጉት ፕሮጀክቶቿ በርካቶችን እንባ እያበሰች፣ ደስታቸውን እየመለሰች ስለመሆኑ አያሌ ምስክሮችን ማንሳት እንችላለን፡፡ ወደ ትናንት ብዙም ርቀን ሳንሄድ በከተማዋ ማዕከላዊ ስፍራ የዶሮ ማነቂያን ያለፈ ጎስቋላ መልክ ስንመለከት በርግጥም ከተማዋ በአቦ ሸማኔ ፍጥነት ራሷን ምን ያህል እያዘመነች እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ ሁሉም ነገር የሚሰራው ለሰዎች ደስታ ነውና ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉ የመዲናዋ ነዋሪዎች ይህንን እውነት ይመሰክራሉ፡፡
ወይዘሮ ሮማን ጌታቸው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በተለምዶ ዶሮ ማነቂያ አካባቢ በልማት የተነሱ ነዋሪ ናቸው፡፡ ባለትዳር እና የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ሮማን በዶሮ ማነቂያ አካባቢ ለ40 ዓመታት ኖረዋል፡፡ አኗኗራቸው ግን ሰው ለመኖር ከሚገባው በታች ነበር፡፡ በአንድ ግቢ ውስጥ ከ20 በላይ አባወራዎችና እማወራዎች ይኖሩ እንደነበር የሚያስታውሱት ወይዘሮ ሮማን በኮምፖርሳቶ እና በካርቶን የተከፈለች የይስሙላ ቤት ውስጥ እየኖሩ አንድን መጸዳጃ ቤት ደግሞ ለ40 ሰዎች እንደሚጠቀሙ በማስታወስ አሁን ግን የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ሁሉ መከራ እንደታደጋቸው ይናገራሉ፡፡

ትናንት በዶሮ ማነቂያ ከቤት ውስጥ ወደላይ ቆጥ ተሰርቶ ሰው እንደዶሮ በቆጥ አልጋ ውስጥ እንኖር ነበር፡፡ ፒያሳ ፊት ለፊት ያማረች ከተማ ብትመስልም ውስጥ ውስጡ ግን ሲኦል ነበር ባይ ናቸው፡፡
ባለቤታቸው ህመምተኛ በመሆናቸው በአልጋ ላይ ይውሉ እንደነበር ገልጸው፣ ከምግብ ቤት የሚያገኟትን ገቢ ለባለቤታቸው የህክምና ወጪ ያወጡም ነበር፡፡ በቀሪ ገቢያቸው ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ፡፡ ከረጅም ጊዜ የአልጋ ቁራኛ በኋላ ባለቤታቸውን በሞት አጥተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ለእነ ወይዘሮ ሮማን ህይወት ፈታኝ ሆኖባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
መኖሪያ ቤታቸው እና አካባቢያቸው ቦታው ጠባብ በመሆኑ እንደፈለጉ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ቤታቸው አልጋ አያዘረጋም ነበር፡፡ አራት ልጆችን ይዞ አልጋ በማታዘረጋ ትንሽ ቤት መኖር ምን ያህል ፈታኝ እንደነበር ጠቁመዋል። ቀን ለሶፋ ማስቀመጫ ማታ ደግሞ ለመኝታነት ይጠቀሙበታል፡፡
ክረምት ፍሳሽ እና ብርድ ይፈራረቅባቸው እንደነበር አስታውሰው፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጆች ይኖሩበታል ተብሎ በማይታሰበው መኖሪያ ቤት ውስጥ እና አካባቢ ህይወታቸውን ይገፉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የጋራ ሽንት ቤታቸው ፈርሶ በባልዲ ይጠቀሙም ነበር፡፡
የሽንት ቤት ሽታ ለጤናቸው ጠንቅ ሆኖባቸው ነበር፡፡ እስከ ቤታቸው ድረስ የሚያስገባው መንገድም ምቹ ባለመሆኑ የታመመ ሰው ወደ ህክምና ቦታ ለማድረስ በጀርባቸው አዝለው ያወጡ ነበር፡፡ ከህክምና ቦታ የሞተ ሰው ደግሞ ወደ ቤት ሳይገባ በዚያው ወደ ቀብር ቦታ ይወስዱ ነበር፡፡ በሰፈራቸው አካባቢ እና በቤታቸው ህይወት ምንያህል ፈታኝ መሆኑን በትዝታ ወደ ኋላ በመሄድ የነበረውን ማህበራዊ ውስብስብ ችግር በአዲሱ ቤታቸው ሆነው አስታውሰዋል፡፡
ዛሬ ወይዘሮ ሮማን ከፒያሳ ዶሮ ማነቂያ አካባቢ በልማት የተነሱ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች በሰባ ደረጃ አካባቢ በተሰራው ምቹ የመኖሪያ ስፍራ አዲስ ሕይወትን እየመሩ ነው፡፡
የዝግጅት ክፍላችን በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ከተማዋ በቅርብ ዓመታት ውስጥ አሮጌ መልኳን እንደ ንስር አድሳ፣ አዲስ ግርማና ሞገስን ተላብሳለች፡፡ አዲስም፣ አበባም ሆናለች፡፡ እነ እሪ በከንቱ፣ እነ ካዛንቺስ፣ እነ ዶሮ ማነቂያ፣ እነ ተረት ሰፈርን የመሳሰሉ አካባቢዎች የትናንት ጎስቋላ መልካቸው እንደ ደመና ተገፍፎ አዲስ ድምቀትን እየተላበሱ ነው፡፡
እነዚያ ጭንቅንቅ ያሉ መንገዶች፣ ጣሪያቸው ያረጀ፣ ማገራቸው የላላ፣ ምሶሷቸው ያዘመመ እና ባለ ላስቲክ ግድግዎቹ የደቀቁ ስፍራዎች በውብ መናፈሻዎች፣ በሰፋፊ መንገዶች እና በሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እየተተኩ ነው። በእርግጥም አዲስ አበባ ገና ከጫጉላ ቤት እንደወጡ ሙሽሮች፣ እንደ ቀይ ሐር ፈትል፣ በለምለም መስክ ላይ እንደሚቦርቁ እንቦሶች እና እንደ ተከፈለ ሮማን ዐይንንም ልብንም እየማረከች ነው፡፡ በዚህ ውበት ውስጥ ደግሞ እየነገሰ ያለ ማህበራዊ ፍትሕ ይታያል፡፡

አንድም የሰዎችን መኖሪያ ምቹ በማድረግ፣ የእለት ጉርስ ለቸገረው ደግሞ ልክ እንደ መማፀኛ ከተማ የሚያገለግሉ የምገባ ማዕከላትን በማቋቋም እንዲሁም ለሀገር ተረካቢው ትውልድ የትምህርት ቤት ምገባን ተግባራዊ በማድረግ፣ ደሳሳ ጎጆዎችን ብቻ ሳይሆን የነዋሪውን መንፈስ በልዩ ልዩ መልኩ በማደስ የተሰሩ ማህበራዊ ፍትሕን ማንገሻ ልማቶችን መጥቀስ እንችላለን፡፡
ለአብነትም በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ አካባቢ የተገነባው የጉለሌ የተቀናጀ ስራን መጥቀስ እንችላለን። ይህ ልማት በዋነኛነት በአካባቢው እንጨት ከጫካ በመልቀም ለሚተዳደሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል የፈጠረ ነው፡፡ መቼም በእንጦጦ ተራራና አካባቢው ወገባቸው በዕድሜና በእንጨቱ ሸክም ጎብጦ የእንጦጦን ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቻቸው ሲሉ የኑሮን አቀበት ሲወጡ ሲወርዱ የነበሩ እናቶች የሚረሱ አይደሉም፡፡
ታዲያ ይህ ፕሮጀክት የታደገው እነዚህን እናቶችና ቤተሰቦቻቸውን ነው፡፡ ማዕከሉ 450 ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ የተገጠመለት፣ ዘመናዊ የሊጥ ማቡኪያ ማሽን፣ ዘመናዊ የአብሲት መጣያ ማሽን እና ሁለት ወፍጮዎች ያሉት ሲሆን፣ ከ550 በላይ እናቶች ወደ ስራ ገብተው በተሻለ የሕይወት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ ቀደም ሲል ከዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ ወገሴ ይናገራሉ፡፡
ባሳለፍነው ሐሙስ (መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም) ደግሞ ሀገራዊ ለውጡ የተበሰረበትን 8ኛ ዓመት አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ድጋፉንም አስመልክቶ አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ “የተሰበሩ ማህበራዊ እሴቶችን በማከም ማህበራዊ ፍትሕ እንዲነግስ የሚያስችሉ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በተለይም በከተማችን የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖችን በተለይም የሀገር ባለውለታዎችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ አካል ጉዳተኞችንና ረዳት የሌላቸውን ወገኖች ከአስቸጋሪ ኑሮ አውጥተን የሰውን ክብር በሚመጥን መልኩ እንዲኖሩ አድርገናል” ብለዋል፡፡
አክለውም፣ “የለውጥ ፍሬዎች ዋንኛ ተጠቃሚ የሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ ማልዶ ወደ አደባባዮች በመውጣት የዘወትር ድጋፉን እንደገና አጽንቷል። ጅማሬያችን ትናንት ቢሆንም ከህዝባችን ጋር ያሳካነው ድል እና የደረስንበት ርቀት ቀላል አይደለም” ብለዋል ከንቲባዋ፡፡
በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ማህበራዊ ፍትሕን የማንገስ ጥረቶችን አስመልክቶ ከአዲስ ልሳን ጋር ቆይታ ያደረጉት በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር አንዋር ጫሚሶ እንደገለፁት፣ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ እንዲህ አይነት ሰው ተኮር ተግባራት ማህበራዊ መስተጋብሩን እውን ለማድረግ እንደሚያግዙና የሀገሪቱን ልማት በተሻለ መሰረት ላይ ለማንበርም ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡
የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ እንደሚሉት ብልፅግናን ለማረጋገጥ እንደ ሀገር ከተቀመጡት የዘላቂ ልማት ግቦች መካከል አንዱ አካታች የሆነ ዕድገት ማምጣት ነው፡፡ ይሄውም ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን ወይም ለተለያዩ ማህበራዊ እና መሰል ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን አካታች በሆነ መልኩ መስራት ሀገራችን አሁን የምታደርገውን ጥረት ምልዑ ለማድረግ ያግዛል፡፡

እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰቡን መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ እየተሰሩ ያል ዘርፈ ብዙ ልማቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን የጠቆሙት የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ አንዋር ጫሚሶ፣ ይህን መሰል ተግባር ቀጣይነት መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥረት ማድረግና ማገዝ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ሶፎንያስ ፍሰሃ በበኩላቸው፣ ከተማዋ በተስፋ ብርሃን እና በተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር፣ በቤቶች ዕድሳት እና ለተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደ ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የመሳሰሉ የማገሚያ እና ወደ አዲስና አዋጭ የሕይወት ምዕራፍ መሸጋገሪያ ማዕከላት ወደ ተግባር በማስገገባት የተጋላጭ ወገኖችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
በቅርቡም በልደታ ክፍለ ከተማ ከተገነባው ዘመናዊ የጂ+4 የመኖሪያ ህንፃ መመረቁ ይታወሳል፡፡ ይህንን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት በልደታ ክፍለ ከተማ የገነባነውን ዘመናዊ የመኖሪያ ህንፃ፣ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ፣ ለአካል ጉዳተኞች እና የሀገር ባለውለታ ለሆኑ ነዋሪዎቻች መተላለፉን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ የልማት ስራዎች ለተነሱ፤ በቀበሌ ቤት ውስጥ በደባልነት፣ በጥገኝነትና በላስቲክ ቤት ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ እንዲሁም የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ በላያቸው እያለፈ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ ወገኖቻችን ጭምር ቤት አስረክበናል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ አዲስ አበባ በሰው ተኮር ስራዎቿ ተምሳሌት እንደሆነችም ተናግሯል፡፡
አክለውም ሰው ተኮር ስራዎችን ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስጀምረው መመሪያ ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 7 ዓመታት በሰው ተኮር እሳቤያችን እና በበጎነት አገልግሎት ተሳትፎ ከ45 ሺህ በላይ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች መገንባት ችለናልም፡፡ ከተማችን ለሁላችንም ትበቃለች፤ መተሳሰብና ፍቅር ካለ ደግሞ ይበልጥ መስራት ይቻላል። በቀጣይም ለብዙዎች ለመድረስ በትጋት እንሰራለን ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡
ሀገራዊ ለውጡ የተበሰረበትን ስምንተኛ ዓመት አስመልክቶ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ባሳለፍነው ሐሙስ (መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም) ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ማህበራዊ ፍትሕን ለማንገስ እና የመዲናዋ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት የሚያደንቁና ለልማቱ ቀጣይነት እገዛቸውን የሚያንፀባርቁ መልዕክቶችንም አስላልፈዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ