በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መሰናዶዎች ይቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል መጽሐፍ፣ የጥበብ አውደ ርዕይ እና የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጻሕፍት
ወጣቱ ደራሲ ናትናኤል ቀረዓለም፣ በዛሬው ዕለት የመጽሐፍ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ያከናውናል፡፡ ይህ የፊርማ መርሃ ግብር የሚካሄደው በቅርቡ በለገሃር ተወልደ ህንጻ ተመርቆ ሥራ በጀመረው አዲሱ የጃዕፈር መጽሐፍ መደብር ሲሆን፣ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 10፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ለአንባቢያን ፊርማውን ያበረክታል። ዝግጅቱ ለሥነ ጽሑፍ አፍቃሪያንና መታደም ለሚፈልጉ በሙሉ ክፍት መሆኑ ተገልጿል። ደራሲው “ዛሬ ቅዳሜ አይደለም”፣ “እውነት አዛምድ” እና “ትናንትና እመጣለሁ” የተሰኙ መጻሕፍትም ለንባብ አብቅቷል።
በሌላ መረጃ “ሮድ ቱ ዲትሮይት” መጽሐፍ ተመርቆ ለንባብ በቅቷል። በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ገደማ የዘለቀ ሙያዊ ተሞክሮ ባላቸው አሸናፊ ጸጋዬ (ዶ/ር) የተጻፈው ይህ መጽሐፍ የዘርፉን የቴክኖሎጂ ሽግግርና የወደፊት አቅጣጫ የሚቃኝ ነው ተብሏል፡፡
መጽሐፉ፣ የአውቶሞቲቭ ዓለም ከተለምዷዊ ሜካኒካል አሠራር ወደ ዘመናዊው የኤሌክትሪክ እና ራስ-አገዝ (Autonomous) ቴክኖሎጂዎች እያደረገ ያለውን ሽግግር በስፋት የሚዳስስ ነው፡፡ በቀጣይ በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለገበያ እንደሚቀርብም ተገልጿል፡፡ አሸናፊ ፀጋዬ (ዶ/ር) በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለ48 ዓመታት በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ በተለይም በዘርፉ በነበራቸው ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የምክር አገልግሎት ይታወቃሉ፡፡
የሥነ ጥበብ አውደ ርዕይ
“በሰማይ እና በምድር መካከል” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ ተከፈተ፡፡ የሰዓሊ መላኩ አየለ ሥራዎች የቀረቡበት ይህ አውደ ርዕይ እስከ ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በዕይታ ላይ ይቆያል። አውደ ርዕዩ የሚታየው ሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ሲሆን መግቢያው በእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በኩል መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሌላ መረጃ “የመንደር ሹክሹክታ፡ ትዝታ እና ንብረት” የተሰኘው የስዕል አውደ ርዕይ በነገው ዕለት ይጠናቀቃል። የሚኪያስ አበራ የግል የሥዕል ኤግዚቢሽን የሆነው ይህ አውደ ርዕይ የማህበረሰቡን አኗኗር፣ ታሪክ፣ ሕይወት እና ተስፋ የሚያሳዩ ሥራዎች የቀረቡበት ሲሆን እየታየ የሚገኘው ቦሌ፣ ብሪቲሽ ኢንተርናሽናል ስኩል አጠገብ ኬኬር ሆምስ 2ኛ ፎቅ በሚገኘው አርታዊ ጋለሪ ውስጥ ነው፡፡
በተጨማሪም የሰዓሊና ቀራጺ ታምራት ገዛኸኝ ሥራዎች የቀረቡበት “ኩይሳ” የቅርጻ ቅርጽ አውደ ርዕይ በዕይታ ላይ ነው፡፡ ይህ አውደ ርዕይ ከተለያዩ የወዳደቁ ቁሳቁሶች የተሰሩ ልዩ የጥበብ ውጤቶች ለተመልካች የቀረቡበት ነው፡፡ አውደ ርዕዩ እስከ ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን ቦታው ደግሞ ብስራተ ገብርኤል፣ ላፍቶ ሞልን አለፍ ብሎ በሚገኘው ሚካኤል ጸጋዬ ክሬቲቭ ስቱዲዮ ነው፡፡
የቴአትር መርሃ-ግብር
“አዮ ቦራ” የአፋን ኦሮሞ የልጆች ቴአትር በህፃናት እና ወጣቶች ቴአትር ቤት ዘወትር ቅዳሜ ከ4:00 ሰዓት ጀምሮ ከልዩ ልዩ ጨዋታዎች ጋር ይቀርባል። “የሰማይ ልጆች” ቴአትር ደግሞ በዚሁ ቴአትር ቤት ዘወትር እሁድ ከ4:00 ሰዓት ጀምሮ ከልዩ ልዩ ጨዋታዎች ጋር ይቀርባል፡፡
በጊዜው አማረ