የአንዲት ዘመናዊ ከተማ ውበት የሚለካው በሰፋፊ መንገዶቿና በረጃጅም ሕንጻዎቿ ብቻ ሳይሆን፣ በስፖርት ዘርፉም ጭምር ነው። ይህንን በተገቢው የተረዳችው አዲስ አበባ፣ የስፖርቱ ዘርፍ እንደ አንድ የመዝናኛ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ከተማ ግንባታና የወጣቶች ሰብዕና መቅረጫ ቁልፍ መሣሪያ ተደርጎ ተወስዷል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአዲስ አበባ የታዩት የመጫወቻ ሜዳና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ናቸው። ከታላላቅ ስታዲየሞች ባለፈ፣ በየአካባቢው የተገነቡትና ዘመናዊ ሰው ሠራሽ ሣር የተነጠፈባቸው ሜዳዎች፣ ስፖርቱ በሰፈር ደረጃ እንዲያንሰራራና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።
ይህ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ስፖርቱን ለሁሉም ተደራሽ ከማድረጉም በላይ፣ ከተማዋ ለታላላቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስፖርታዊ ኩነቶች ዝግጁ እንድትሆን አድርጓታል ማለት ይቻላል። እዚህ ጋር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ለማዘጋጀት ዕድል ማግኘቷን በማሳያነት ጠቅሰን እንለፍ። በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር እና የወንዞች ዳርቻ ልማት ሥራዎች ከስፖርት እንቅስቃሴ ጋር በቅርበት የተሳሰሩ ናቸው። ለብስክሌት መንዳትና ለእግር ጉዞ የተዘጋጁ መንገዶች እንዲሁም በፓርኮች ውስጥ የተካተቱ የስፖርት መገልገያዎች አዲስ አበባን የስፖርት ከተማ ለማድረግ የታለሙ ናቸው።
የስፖርት ተንታኞችና የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት፣ አዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለስፖርቱ የሰጠችው ትኩረት ከወትሮው የተለየና ስልታዊ ነው። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፣ ስፖርት ከሜዳ ላይ ውድድር ባለፈ የከተማዋን ገጽታ በመገንባት፣ የቱሪስት መስብህ በመሆንና ወጣቶችን ከሱሰኝነትና ካልተገቡ ተግባራት በመታደግ ረገድ የላቀ ሚና አለው። በተለይም በኮሪደር ልማት ውስጥ የተካተቱት የብስክሌትና የእግር ጉዞ መንገዶች፣ እንዲሁም በየሰፈሩ የሚገነቡ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ጤናማ እያደረጓት መሆኑን ይገልጻሉ።
የመዲናዋ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በአብዛኛው ተለውጠዋል በሚለው አስተያየት የ“አዲስ ተስፋችን” እግር ኳስ ፕሮጀክት መሥራችና አሰልጣኝ መሐመድ ናስር ይስማማል። “የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የአዳጊና ወጣት ፕሮጀክቶች ስፖርቱን ለማስፋፋትና ለማሳደግ ዋነኛ መሠረቶች ናቸው” የሚለው አሰልጣኝ መሐመድ፣ አሁን ላይ በመዲናዋ በሲኤምሲ አካባቢ ከ7 እስከ 17 ዓመት ያሉ አዳጊዎችን በፕሮጀክት አቅፎ በማሰልጠን ላይ ይገኛል። “የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በአሳሳቢ ሁኔታ እየቀነሱ ነው” የሚለው ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረው ቅሬታም መፍትሔ እያገኘ ስለመሆኑ ያስረዳል።
በተለይም ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርትን ከከተማዋ ውበትና ከነዋሪዎች ጤና ጋር በማስተሳሰር፣ ንቁና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የጀመረው ሥራ፣ ዛሬ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያሉ አንጋፋ ክለቦችን ከመፍረስ እስከ መታደግ የደረሰ ሰፊ እይታ ያለው መሆኑን ያረጋግጣል። የከተማ አስተዳደሩ ለስፖርቱ የሰጠው ትኩረት በግንባታ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ የክለቦችን ተወዳዳሪነትና የፋይናንስ አቅም ለማጠናከርም ልዩ ልዩ ስልቶችን ሲተገብር ቆይቷል።
በተለይም በከተማዋ ሥር የሚገኙ ክለቦች በበጀት እጥረት ሳይንገላቱ ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ የሚደረግበትን አሠራሮች ዘርግቷል። አሁን ላይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የተደረገው ድጋፍም የዚሁ ዕቅድ አካል ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ የግሉ ዘርፍ በስፖርቱ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርግና በስፖርት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በማነቃቃት ረገድ የላቀ ሚና ተጫውቷል። ይህ ጥረትም ክለቦች ራሳቸውን ችለው በጠንካራ የፋይናንስ መሠረት ላይ እንዲቆሙና የከተማዋን ዝና በዓለም አቀፍ መድረክ እንዲያሳድጉ ያለመ ነው።
ባለፉት ሰማንያ ዘጠኝ ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ መተንፈሻ ሳንባ ሆኖ የዘለቀው ይህ ፈር ቀዳጅ ክለብ፣ ከገጠመው የፋይናንስ ችግር የተነሳ ሕልውናው አደጋ ላይ ወድቆ ሰንብቷል። ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ታሪክ አይፈርስም” በሚል በወሰደው ቁርጠኛ እርምጃና ባሰባሰበው የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ፣ የክለቡን መጻኢ ዕድል ብሩህ የሚያደርግ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ባለፈ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ ልብ ውስጥ የሚኖር ትልቅ ሰብዕና ነው። ክለቡ የገጠመው የፋይናንስ ቀውስ በደጋፊው ዘንድ የፈጠረው ሥጋትና ጭንቀት ቀላል ባይሆንም፣ የመንግሥት ድጋፍ ግን የደጋፊውን ተስፋ መልሶ ያለመለመ ሆኗል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እንደገለጹት ይህ ድጋፍ ከገንዘብ በላይ የከተማዋን የስፖርት ወግ የመጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት መገለጫ ነው።

አዲስ አበባ በኮሪደር ልማትና በመሠረተ ልማት ግንባታ አዲስ መልክ እየያዘች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ የከተማዋን ስም የሚሸከሙ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያሉ አንጋፋ የእግር ኳስ ክለቦች መዳከም ለከተማ አስተዳደሩ የማይታለፍ ጉዳይ ሆኗል። መንግሥት ለክለቡ ሕልውና ማስቀጠያ ፈሰስ ያደረገው 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ፣ የከተማ ግንባታ ሥራ ከድንጋይና ከኮንክሪት ባለፈ ማኅበራዊ እሴቶችን መታደግ መሆኑን ያረጋገጠበት ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።
ለወራት የዘለቀ የደመወዝ እጦት፣ የተጫዋቾች መበተን ሥጋትና የክለቡ ደጋፊዎች ጭንቀት… የታሪካዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ሰማይ ላይ ያንዣበበው ጥቁር ደመና በመንግሥትና በባለሀብቶች የተቀናጀ ጥረት ሊገፈፍ ችሏል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሪነቱን ሚና በመውሰድና የግል ኢንቨስትመንት ግዙፎችን በማስተባበር ያበረከተው የገንዘብ ድጋፍ፣ ክለቡን ከመፍረስ አፋፍ ከመታደጉም በላይ ወደ ቀድሞ ክብሩ የሚመለስበትን በር ከፍቶለታል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹትም ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለብ የተጫዋቹ እና የማኅበሩ ብቻ ሳይሆን የከተማዋ ጠንካራ ክለብ ነው። “በመሆኑም ይህንን አገራችንን እና ከተማችንን የወከለ ታሪካዊ የስፖርት ክለብ ከመፍረስ የመታደግ ኃላፊነት እንዳለብን እናምናለን” ብለዋል።
ከንቲባዋ አያይዘውም ይህ አንጋፋ የስፖርት ክለብ ላለፉት 6 ወራት ደመወዝ መክፈል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ እና የመበተን አደጋ ተጋርጦበት መታየት ስለሌለበት የከተማ አስተዳደሩን በጀት በመወሰን፣ ለባለሀብቶች በቀረበው ጥያቄ መሠረት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ቢጂአይ ኢትዮጵያ በሰጡን ፈጣን ምላሽ በጥቅሉ የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ ስለማስረከባቸው ገልጸዋል።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ “ይህ ድጋፍ አስተዳደራችን ክለቡን ከውድቀት ለመታደግ እና ለስፖርት ወዳድ ሕዝብ የሰጠው ክብር አንዱ ማሳያ ሲሆን፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለብ ሁሉንም ባሳተፈ እና በግልጽነት አዲስ ቦርድ መርጦ ከገጠመው ጊዜያዊ ችግር ተላቅቆ ወደ ቀድሞ ጥንካሬውና ዝናው የሚመለስበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን እመኛለሁ” ብለዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት “ክለባችን የገባበትን ችግር ተረድተው ትኩረት በመስጠት ለሰጡን ድጋፍ እና ቆራጥ አመራር እናመሰግናለን። ክብርት ከንቲባ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪካዊነት እና ስላለው ዋጋ በተገቢው መልኩ በመረዳትዎም ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው” ብሏል።
አያይዞም “ራሳችንን የኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ ክለብ ነን ብለን ስንጠራም በእንዲህ ዓይነት ቀን ከተማችን ከጎናችን እንደምትሆን በማመን ነበር፤ በእርስዎ ተግባር አዲስ አበባ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆናቸውን አረጋግጠናል” የሚል መልዕክትም አስተላልፏል።
ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ ሥራው የሚጠናቀቀው ስፖርታዊ ማዘውተሪያዎች በታሪካዊ ክለቦች ሲሞቁ ነው። የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የተጫዋቹ እና የማኅበሩ ብቻ ሳይሆን የከተማዋ የጥንካሬ መገለጫ ነው። ይህ 100 ሚሊዮን ብር ለክለቡ የተሰጠ ገንዘብ ብቻም ሳይሆን የከተማዋ አስተዳደር ለስፖርት ወዳዱ ሕዝብ ያለውን ክብርና ተቆርቋሪነት በተግባር ያሳየበት ነው። እግር ኳስ ክለቡ ሁሉንም ባሳተፈ እና በግልጽነት አዲስ ቦርድ መርጦ ከገጠመው ጊዜያዊ ችግር ተላቅቆ ወደ ቀድሞ ጥንካሬውና ዝናው የሚመለስበት ጊዜ ቅርብ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በሳህሉ ብርሃኑ