ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአዲስ ስፖርት ፓርክን መረቁ

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአዲስ ስፖርት ፓርክን መረቁ

AMN — መጋቢት 26 /2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የከተማ እድሳትን ለማፋጠን እና የዜጎችን ክብር ለመመለስ ከተገባው ቃል መካከል አንዱ የሆነውን የአዲስ ስፖርት ፓርክን በይፋ መርቀው ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ይህ ፕሮጀክት ዘመናዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘው ቁርጠኝነት ጉልህ ማሳያ ነው።

በ5.7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ማዕከል፣ ለሀገራችን በኦሎምፒክ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ 15 አትሌቶችን የሚዘክሩ ሐውልቶች በክብር ቆመውበታል።

ይህም የጀግኖቻችን ታሪክ ለተተኪው ትውልድ ስፖርተኞች ዘላቂ ተምሳሌት እንዲሆን ታስቦ የተከናወነ ነው።

ማዕከሉ እያንዳንዱ ክፍሉ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟላ ተደርጎ የተገነባ ሲሆን፤ የኦሎምፒክ ደረጃውን የጠበቀ የመዋኛ ገንዳ፣ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የሜዳ ቴኒስ ሜዳዎችን እና የ800 ሜትር የሩጫ ትራክን አካቷል።

“የእውነተኛ ልማት ማዕከል ማህበረሰቡ ሊሆን ይገባል” የሚለውን መርህ በመከተልም፣ በልማቱ ምክንያት ለተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ አቅም የሚሆኑ 105 አዳዲስ የንግድ ሱቆች ተገንብተዋል።

በተጨማሪም 3 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ ፕላዛ፣ የ300 መኪናዎች ማቆሚያ እና ከወንዝ ዳርቻ ልማት ጋር የተሳሰረ ውብ አካባቢን ይዟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፤ ታላቋን ኢትዮጵያ ማለም ብቻ ሳይሆን በተግባር በመገንባት ላይ መሆናቸውን በድጋሚ አረጋግጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review