AMN -መጋቢት 26/2018ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲሱ ስፖርት ፓርክ ስፖርታዊ ክህሎትን ከማሳደግ ባለፈ፣ ለትውልድ ማህበራዊ ትስስር እና ለነገዋ ኢትዮጵያ ስኬት መሰረት የሚጥል መሆኑን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘመናዊ መልክ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን የስፖርት ፓርክ በመረቁበት ወቅት ፣ ሀገርን የመገንባት ስራ የሚጀምረው “ሰውን ከመስራት” መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተገነቡትን 35 ሺህ የሚጠጉ የህፃናት መዋያዎችን እንደ ምሳሌ በማንሳት፣ ትኩረት መደረግ ያለበት በመሠረታዊ የትምህርት እርከኖች ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ነገ ያለው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ስራው ከመሰረቱ መጀመር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ከቀለም ትምህርት ባሻገር ሀገርን ለመገንባት የቀለም ትምህርት እና ፈተና ማለፍ ብቻውን በቂ አለመሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዐቢይ፣ “ሰው የሚሰራው ከሰው ጋር ሲዋሃድ፣ ሲረዳዳ እና የራሱን መብት ማስከበር ሲችል ነው” ብለዋል።
አዲሱ ስፖርት ፓርክ ህፃናትና ታዳጊዎች በጋራ እየተጫወቱና እየሰለጠኑ ማህበራዊ ትስስርን እንዲማሩ ታስቦ የተገነባ መሆኑንም አክለዋል።
የጀግኖች አርአያነት እና የወደፊት ተስፋ ፓርኩ የነአበበ ቢቂላ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ቀነኒሳ በቀለ እና ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ የሌሎች የኢትዮጵያ ጀግኖች ሃውልትና ታሪክ የተዘከረበት ነው። ይህም ታዳጊዎች እነዚህን ጀግኖች በአርአያነት እያዩ እንዲያድጉ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል።
“ሳንዘራ ማጨድ አንችልም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኦሎምፒክ ደረጃ የተገነቡት የዋና እና ሌሎች የስፖርት ማዘውተሪያዎች ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ስሟን የሚያስጠሩ አዳዲስ ጀግኖችን እንድታፈራ ያስችላታል ብለዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ