የሆሣዕና በዓል ምስጢራዊ ትርጓሜ እና የሕማማት ሳምንት መንፈሳዊ ሥርዓቶች

You are currently viewing የሆሣዕና በዓል ምስጢራዊ ትርጓሜ እና የሕማማት ሳምንት መንፈሳዊ ሥርዓቶች

AMN – መጋቢት 27/2018 ዓ.ም

የሆሣዕና በዓል የሰው ልጅ ለዘመናት ሲጠባበቀው የነበረ የመዳን ተስፋ የተፈጸመበትና ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ታላቅ ዕለት መሆኑን የሀይማኖት አባቶች ያስረዳሉ።

በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የስብከተ ወንጌል ኃላፊ መጋቢ ሐዲስ ባሕረ ጥበብ አዱኛ ከAMN ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሠረት “ሆሣዕና” የሚለው ቃል “አሁን አድን” ማለት መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ለ5 ሺህ 500 ዘመናት በጨለማ የነበረው የሰው ልጅ የነፃነትና የመዳን የምስራች መሆኑን አብራርተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለቱ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተጭኖ በዘንባባ ዝንጣፊ ታጅቦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ፣ በብሉይ ኪዳን የነበረውን የጦርነት ምልክት ወደ ሰላም የለወጠ ነው ብለዋል።

ክርስቶስ በሰው ዘንድ ዝቅ ተደርጋ የምትታይ አህያን መምረጡ ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እኩል መሆኑን የሚያመለክት መሆኑንመጋቢ ሐዲስ አስታውሰው፤ ይህም የታሰሩት ሁሉ የሚፈቱበት የነፃነት ዘመን መድረሱን የሚያበስር መሆኑን ገልጸዋል።

በዕለቱ የሚከናወኑ የቤተክርስቲያን ሥርዓቶችም ይህንኑ ምስጢር የሚያንጸባርቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በአራቱ ማዕዘናት ወንጌል የሚነበብበት ዑደት እና “አርኅዉ” በመባል የሚታወቀው ሥርዓት ለዘመናት ተዘግቶ የነበረው የገነት ደጅ መከፈቱን በምልክት የሚያሳይ መሆኑንም አብራርተዋል።

ከሆሣዕና ማግስት ጀምሮ እስከ ስቅለት ያሉት የሕማማት ቀናት የሟች ፍትሐት የማይከናወንባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ቤተክርስቲያን በዚህ ጊዜ ለምእመናን በሕይወታቸው እያሉ የኃጢአት ምስጢር መፍቻ ፀሎት የምታከናውን ልዩ ሥርዓት እንዳላት አስረድተዋል።

ከሆሣዕና በኋላ የሚጀመረው የሕማማት ሳምንት የክርስቶስን መከራና ስቃይን የሚታሰብበት መንፈሳዊ ወቅት ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት ምእመናን የሚያደርጉት መንፈሳዊ ጥንቃቄ ልዩ መሆኑንመጋቢ ሐዲስ ገልጸዋል።

በተለይም ይሁዳ ጌታን በመሳም አሳልፎ የሰጠበትን ክህደት ለማስታወስ፣ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ከመሳሳም እንደሚቆጠቡ አጽኖት ሰጥተዋል።

በመጨረሻም መጋቢ ሐዲስ፤ ሳምንቱ ከብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን የሚያሸጋግር ወቅት በመሆኑ፣ እስከ ትንሳኤ ድረስ ከደስታ መግለጫዎች በመራቅ፣ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት እንዲያሳልፉ ለምእመናን ጥሪ አቅርበዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review